Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ከ‹‹National Institute of Technology›› ጋር በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ‹‹Application of Novel Techniques for Waste Water Treatment›› በሚል ርዕስ ሚያዝያ 21/2014 ዓ/ም ኦንላይን ሴሚናር አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ እንደገለጹት ሴሚናሩ ሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ያደረገ ሲሆን መምህራንና የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ምርምሮችን በጥያቄና መልስ ዕውቀት ለመጋራትና ቤተ-ሙከራዎችን ለማደራጀት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ከሀገር ውጪ ሄደው ምርምሮችን መሥራት የሚችሉበት እና በቀጣይ ትስስሩ የሚጠናከርበት መንገድ ላይም ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኬሚስትሪ ት/ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ አትጠገብ አበራ ሴሚናሩ ከኢንደስትሪዎች የሚወጡ የተበከሉ ፈሳሾች አካባቢያችንን፣ ሰዎችንና እንስሳትን እንዳይጎዱ አዳዲስ ቴክኒኮችን በመጠቀም አረንጓዴና ንጹህ አካባቢን መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሴሚናሩ በየሳምንቱ መጨረሻ የሚከናወን ሲሆን መሰል ልምዶችን ማስቀጠል ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለንን ግንኙነት ያጠናክራልም ብለዋል፡፡

የት/ክፍሉ መምህርና የሴሚናሩ አስተባባሪ ተ/ፕ ዶ/ር ራምሽ ቡርማሴ (Rameshi Burmase) በበኩላቸው ከፋብሪካ የሚወጡ ፈሳሾችን እንዴት ማከም እንደሚቻል በሴሚናሩ የተዳሰሰ መሆኑን ገልጸው የተበከለ ውሃ የማከም ዘዴ ለጨርቃ ጨርቅና ለስኳር ፋብሪካዎች እንዲሁም ለተለያዩ ኢንደስትሪዎች ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮግራሙ ለተመራማሪዎች፣ ለቅድመና ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም በዘርፉ ጥናት ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ ሴሚናሩ በቀጣይ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎችን በማካተተ የሚከናወን መሆኑንም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት