Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቪታ/Vita/ ከተሰኘ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት የተሻሻሉና ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በጋሞ ዞን ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ለማዳረስ በሚሠራው ፕሮጀክት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ሚያዝያ 28/2014 ዓ/ም ለ5 ዓመታት የሚቆይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በመክፈቻ ንግግራቸው የአየር ንብረት ለውጥ አሁን ላይ ዓለምን በእጅጉ እየፈተነ ያለ ችግር መሆኑን ጠቅሰው በዋናነትም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት በአብዛኛው የችግሩ ገፈት ቀማሾች ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ቪታ በ5 ዓመታት ውስጥ አራት መቶ ሺ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በጋሞ ዞን ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማዳረስ በሚል የቀረጸው ፕሮጀክት በጉልህ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታና ከአካባቢ ጥበቃ አንፃርም የጎላ ፋይዳ ያለው ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት የሚጠበቅበትን ሁሉ በትጋት ይወጣል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቪታ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኩሪያ በበኩላቸው ድርጅታቸው የአየር ንብረት ለውጥን የመዋጋትና በኢትዮጵያና ኤርትራ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የአኗኗር ሁኔታን የማሻሻል ተልዕኮን አንግቦ እየሠራ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው ድርጅታቸው እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ በኢትዮጵያ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልልና በአማራ ክልል በሚገኙ 7 ዞኖች ላይ ተልዕኮውን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ድርጅቱ “Vita Green Impact Fund” በተሰኘ ፕሮግራሙ በጋሞ ዞን ገጠራማ ክፍል ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከአካባቢ ጥበቃና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተስማሙ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማቅረብ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከዚህም አንፃር ለፕሮጀክቱ መሳካት የምርምርና የፈጠራ ሃሳቦች ምንጭ ከሆነው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳችን ለፕሮጀክቱ ስኬት የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በስምምነቱ እንደተመለከተው ዩኒቨርሲቲውና ድርጅቱ የተሻሻሉ የማገዶ ምድጃዎችን ማኅበረሰብ መር ዘዴን በመከተል የሚከናወነውን የቴክኖሎጂውን ማሰራጨት፣ ማላመድና ማስተዋወቅ ሂደት ዙሪያ፣ በማኅበረሰብ መር ልማት ዙሪያ አዳዲስ ሃሳቦችን ማመንጨት ላይ፣ የተሻሻሉ የማገዶ ምድጃዎች ማላመድ ዙሪያ የሚገጥሙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባዮ-ፊዚካል ተግዳሮቶችን መለየት ላይ፣ በማኅበረሰብና ቤተሰብ ደረጃ የተሻሻሉ የማገዶ ምድጃዎች ማላመድ ዙሪያ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አመለካከቶችንና ባህሪያትን መለየትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የትብብር ጥናቶችን ያከናወናሉ፡፡

በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው ቪታ በቀጣይ 5 ዓመታት ውስጥ ጋሞ ዞንን ከሶስት ጉልቻ መጠቀም ነፃ ለማድረግ አራት መቶ ሺህ የተሻሻሉና ማገዶ ቆጣቢ የመቀቀያና የመጋገሪያ ምድጃዎችን ማኅበረሰብ መር የአሠራር ዘዴን በመጠቀም ለማዳረስ የሚሠራ ሲሆን ይህም ሥራ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከጤናና በሴቶች ላይ የሚስተዋለውን የሥራ ጫናና ፆታዊ ጥቃቶችን የሚቀንስ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ከዚህም አንፃር ቴክኖሎጂውን ለማኅበረሰቡ በማዳረስ ሂደት ውስጥ አዳዲስ ሃሳቦችንና የተሻሻሉ አዳዲስ ፈጠራዎችን ከማመንጨት ረገድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለይም በዩኒቨርሲቲው የሚገኘው የታዳሽ ኃይል ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅበት አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት