Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከአርባ ምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ እና ከአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በከተማው ስድስት ቀበሌያት ውስጥ ከሚገኙ 12 ቀጠናዎች ለተወጣጡ 66 አመራሮችና 80 የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች አደረጃጀት አባላት ሚያዝያ 27/2014 ዓ/ም የአመራርነት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥልጠናው ዓላማ ሴቶችና ወጣቶች ያለባቸውን የአመራርነት ክሂሎት ክፍተት በመሙላት በተሰማሩበት መስክ አፈጻጸማቸው እንዲሻሻል በማድረግ ብቁ መሪዎችን ማፍራት መሆኑን የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ስለሺ አበበ ገልጸዋል፡፡

ሴቶች በየተሰለፉበት የመሪነት ቦታ ሀገርን ለመገንባት የበኩላቸውን ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን የገለጹት የአርባ ምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ተስፋጽዮን ዘነበ በያለንበት ደረጃና ቦታ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መቋቋምና ችግሮችን መሻገር የምንችልበትን ዘዴ ተነጋግሮ በመፍታት የአንድነት ማዕከላችንን ማስጠበቅ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ ሴቶች የችግሮች መፍቻ ሃሳብ አመንጪ እንደመሆናቸው መጠን አሁን ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ ተቋቁመው ለመወጣት ጠንካራ ስነ-ልቦና ሊገነቡ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህር አቶ አበበ ዘየደ አመራርነት አዎንታዊ ተጽዕኖዎችን በመፍጠር የሰውን አመለካከትና ባህርይ ወደ ራስ መሳብ፣ ማኅበረሰቡን መደገፍና ማበረታታት እንዲሁም ባለሙያዎች በአግባቡ እንዲያገለግሉ አቅጣጫ ማሳየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወደ አመራርነት ለመምጣት መጀመሪያ ራስን ማብቃት ያሻል ያሉት መ/ር ዘየደ ሴቶች ከቤት ማስተዳደር ጀምሮ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውና የአመራርነትን ሚና የተላመዱ በመሆኑ በተለያየ የሥራ መስክ ላይ ሲቀመጡ የተለያዩ አፋጻጸሞች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንጻር ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ያለባቸውን ጫና ተረድቶ ማሠልጠን፣ ከጎናቸው መሆን፣ ኃላፊነት መስጠትና እንዲበቁ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የት/ክፍሉ መምህር አቶ ቢክስ ሰጠኝ የአመራርነት ባህሪያቶችን አስመልክቶ በሰጡት ሥልጠና አንድ አመራር አመራር ሊሰኝ የሚችለው በዙሪያው ካለው ማኅበረሰብ ዕውቀትን ለመማር ራሱን ዝግጁ ሲያደርግ ብሎም ማንበብና ማወቅ ብቻ ሳይሆን ያወቀውን ትክክለኛ ነገር መተግበር ሲችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ቢክስ ስሜትን መቆጣጠር መቻል፣ የሰዎችን ባህርይ መረዳት፣ ችግር ሲገጥም በሌሎች ቦታ ሆኖ ማሰብ፣ ሰዎችን መምራትና መደገፍ፣ ማነሳሳት፣ ሠርቶ ማሳየት፣ በሠራተኛውና በአመራሩ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ፣ ተከታዮችን ማፍራት፣ በሁሉም ነገር የተሻለ ሰብዕና ያለው ሆኖ መገኘት እንዲሁም ጥሩ ማንነት መገንባት የአመራርነት አንዱ መገለጫ ሲሆኑ ሠልጣኞች የአመራርነት ባህሪያቱን በመላመድ እንዴት በራሳቸው ላይ ሊተገብሩ እንደሚችሉ በሥልጠናው ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

የአ/ም/ከ/ብ/ፓ/ሴ/ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አብነት ተስፋዬ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት ሴቶች ውሳኔ ሰጪ እንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ያላቸውን እምቅ ዕውቀት ካገኙት ሥልጠና ጋር በማዋሐድ ወደ ኅብረተሰቡ ወርደው ሊሠሩበት እና በቤታቸውና በአካባቢያቸው ጥሩ መሪ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ሥልጠናውን ላላገኙ አመራሮች ሥልጠናው እንደሚሰጥ የተናገሩት ኃላፊዋ ዩኒቨርሲቲው ሥልጠናውን አዘጋጅቶ በመስጠቱ አመስግነዋል፡፡

ሠልጣኖች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን የክሂሎት ክፍተት ከመቅረፉና በቀጣይ እንዴት መምራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ከማሳየቱ ባሻገር በተሰለፉበት መስክ ስኬታማ እንዲሆኑ የሚረዳቸው መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲውንና አሠልጣኞቹን አመስግነዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት