የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ምቹ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ በተመሠረተው ዓለም አቀፍ ድርጅት ‹‹Vita›› ስር በኬኒያ ሀገር የተቋቋሙት የ‹‹Dream Team›› አባላት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተቋቋሙት አቻ የ‹‹Dream Team›› አባላት፣ ለግብርና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ከሚያዝያ 24-26/2014 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ‹‹PlantVillage›› እና ‹‹PlantVillageNuru›› ሶፍትዌር መተግበሪያ (Software Application) አጠቃቀም ዙሪያ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው በዋናነት በበሽታ የተጠቁ እና ያልተጠቁ ሰብሎችን የሞባይል ሶፍትዌር መተግበሪያን በመጠቀም መለየትና በ24 ሰዓት ውስጥ በበሽታ ለተጠቁ ሰብሎች መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ‹‹Plant Village›› የሚባል አዲስ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ቴክኖሎጂው ወደ ሀገራችን መምጣቱ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የግብርና አሠራር ጋር በማቀናጀት ግብርናውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት፣ ልምድ ለመለዋወጥ፣ ምርቱን ውጤታማ ለማድረግና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ለመስጠት ይረዳል ብለዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለወጡና ለሌሎች ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

የቪታ የ‹‹Agricultural Land Program›› ማኔጀርና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ መስፍን ከበደ የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፣ የተሻሉ ተሞክሮዎችና የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ በትብብር የሚሠሩትን በመደገፍ ካመረቱት ምርት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ዕድል መፍጠርና የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ተቋማቸው በዋናነት ትኩረት በመስጠት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ተጽዕኖ ለመከላከል አርሶ አደሮች የኃይል አማራጭ እንዲኖራቸው የተለያዩ ዘመናዊ ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ራሳቸው አምርተው እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረጉና ጤናቸው እንዲጠበቅ ተቋማቸው ድጋፍ እንደሚሰጥ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

የቪታ የጋሞና ጎፋ ዞኖች ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ፀሐዩ ካሴ ተቋሙ በአርባ ምንጭ አካባቢ ላለፉት 16 ዓመታት በተለያዩ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸው በተለይ በደጋና ቆላማ አካባቢዎች የተለያዩ የዘር ብዜቶችን በስፋት እያቀረበ እንዳለና እስከ አሁን ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በዞን ደረጃ በተካሄደው የአረንጓዴ ልማት ሽልማት ላይ ከ50-60 በመቶ የሚሆኑ አርሶ አደሮች የቪታ ተጠቃሚ ሲሆኑ በተለይ ዘመናዊ የሞባይል ስልክ የያዙ አርሶ አደሮች አጠቃቀሙን በቀላሉ በመረዳት ሰብሎችን ከበሽታ ማዳን ይችላሉ፡፡

ቪታ ከዚህ ቀደም በሶማሊያ አካባቢ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችን ለማቅረብ በአዬርላንድ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ከጀመረበት 2000 ዓ/ም ጀምሮ ከ14 ዓመታት በላይ በተለይ ከድርቅና ከግብርና ሥራ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችንና ሌሎች እርዳታዎችን ሲያደርግ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በኤርትራ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ከምርምር ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር መሰል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሠልጣኞች በአርባ ምንጭ ዙሪያ ጋንታ ካንቻሜ ቀበሌ በእርሻ ማሳ ውስጥ የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም በአዲሱ የሶፍትዌር መተግበሪያ በቀላሉ በበሽታ የተጠቁና ያልተጠቁትን የካሳቫና የበቆሎ ሰብሎችን ለመለየት የቻሉ ሲሆን በሥልጠናው ማጠናቀቂያም የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በሥልጠናው በኢትዮጵያ የቪታ አስተባባሪዎችና አመራሮች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪዎች፣ ከጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ እና ከአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳና ከጨንቻ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤቶች የመጡ ባለሙያዎች፣ ከጋሞ ዞን የተመለመሉ የDream Team አባላት እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ከቪታ የመጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት