የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የእግር ኳስ ክሂሎት ላላቸው በአርባ ምንጭ አካባቢ ከሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ማዕከላትና ትምህርት ቤቶች ለተመለመሉ ከ17 ዓመት በታች ለሆኑ 60 ታዳጊዎች ሚያዝያ 28/2014 ዓ/ም የተለያዩ የእግር ኳስ ቁሳቁሶችን አበርክቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ድጋፉ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለከተማዋ የስፖርት እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ከማድረግ በተጨማሪ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡

ዶ/ር ዓለማየሁ ታዳጊዎቹ በትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን የቀለም ትምህርት ከስፖርት እንቅስቃሴው ጎን ለጎን ማስኬዳቸው የከተማዋን እግር ኳስ ክለብ በክሂሎታቸው ከማገዝ ባለፈ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ የሀገራቸውን እግር ኳስ በትልቅ ደረጃ ለማስጠራት ጠንክረው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ከተማ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፉ ለአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው ማኅበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው አካዳሚውም በስፖርቱ ዘርፍ ማኅበረሰቡን ለማገልገል መሰል ተግባራትን ለማከናወን በዕቅድ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ታዳጊዎች በእግር ኳስ ያላቸውን ፍላጎትና ክሂሎት ተጠቅመው ለከተማው ክለብ አጋዥ እንዲሆኑና ለሀገራችን እግር ኳስ ዕድገትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻልና ለማበረታታት የስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁሶቹ መበርከታቸውን አቶ አሰግድ ጠቁመዋል፡፡

ማሊያዎች፣ የእግር ኳስ ጫማዎች፣ ቅልጥም መከላከያዎች (መጋጫዎች)፣ የልምምድ ልብሶችና የእግር ኳሶች ከተበረከቱ ቁሳቁሶች መካከል ሲሆኑ አጠቃላይ የቁሰቁሶቹ ወጪ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን አቶ አሰግድ ገልጸዋል፡፡

ከመስከረም 2012 ዓ/ም ጀምሮ ከፕሮጀክት ማሠልጠኛ ማዕከላት፣ ከትምህርት ቤቶች እንዲሁም ፍላጎትና ክሂሎት ካላቸው ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተመለመሉት ከ500 በላይ ታዳጊዎች መካከል የእግር ኳስ ክሂሎት ያላቸው ወንድ 30 እና ሴት 30 በአጠቃላይ ለ60 ታዳጊዎች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ታዳጊዎቹ ድጋፉን ከዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ከሆኑት ከዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እጅ ተረክበዋል፡፡