Print

የዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ለዓባያ፣ ጫሞና ነጭ ሳር ካምፓስ የአስተዳደር ሠራተኞች የጾታና የሥርዓተ ጾታ ምንነት፣ የጾታዊ ጥቃቶች ምንነትና ዓይነቶች፣ ጾታዊ ጥቃቶችን መከላከያ መንገዶች እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከግንቦት 02-03/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለማስቆምና እኩል ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የሁለቱንም ጾታ ጠንካራ የሥራ ባህል ለማዳበር ታልሞ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በሥርዓተ ጾታ ጉዳይ የተዛቡና ስር የሰደዱ ኋላ ቀር አመለካከቶችን በአንድ ጊዜ ለማስቀረት የማይቻል በመሆኑ ተከታታይነት ያላቸው ሥልጠናዎችን በመስጠትና ማኅበረሰቡን በማስተማር ተጋላጭነቱን መቀነስ እንደሚቻል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሴቶች ተሳትፎ ለሀገር ልማት የላቀ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ ሴቶች በራስ መተማመናቸውን በማጎልበትና ክፍተቶቻቸውን ለይተው ራሳቸውን በዕውቀት በማነጽ በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ወ/ሪት ሠናይት አሳስበዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ጾታዊ ጥቃቶችን በባለቤትነት ስሜት መመልከትና ጉዳዩን በማስረጃ አስደግፎ ለሕግ በማቅረብ ውሳኔ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ማርሸት ማቴዎስ በበኩላቸው የተዛባ የሥርዓተ ጾታ አመለካከት ሴቶች ለአላስፈላጊ የሥራ ጫና እንዲዳረጉ፣ የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸውና ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡ አመለካከቱ ለቀጣይ ትውልድ እንዳይሻገር ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣትና ግንዛቤን በመፍጠር መቀየር እንደሚቻል ባለሙያዋ ጠቁመዋል፡፡

ጾታዊ ጥቃቶች በቃልና በተግባር ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የተናገሩት ሌላኛው የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያና አሠልጣኝ አቶ ታደለ ሸዋ ሴቶችን አሳንሶ ከማየት በሚመነጭ የተሳሳተ አመለካከት እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ባለመያዝ ጾታዊ ትንኮሳዎች እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጫና የሚያስከትል መሆኑን ጠቅሰው ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቀነስ ለራስ ዋጋ መስጠት፣ ከአደንዛዥ ዕጾች መቆጠብና ተጋላጭነትን መቀነስ ይገባል ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች በአስተያየታቸው በሥልጠናዎችና በትምህርት የተዛቡ አመለካከቶች መሻሻል እያሳዩ መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ሥልጠናውን ለሁሉም ተደራሽና ቀጣይነት ያለው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት