Print

AMU-IUC ፕሮግራም ለሁለተኛ ዙር ላወጣው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል አመልካች ሴት መምህራን ግንቦት 4/2014 ዓ/ም የማነቃቂያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የAMU-IUC ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት IUC ፕሮግራም ለሁለተኛ ዙር ላወጣው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ውድድር እስከ አሁን ባለው መረጃ የወንድ አመልካቾች ቁጥር 44 ሲሆን 5 ሴቶች ብቻ አመልክተዋል፡፡ የወንድ አመልካቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ዶ/ር ፋሲል የሴቶች ተሳትፎ ከሚጠበቀው በታች ሆኖ በማግኘታቸው ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ውይይት የሴት አመልካቾችን ቁጥር ለመጨመር ይረዳቸው ዘንድ የማመልከቻው ቀን ለ1 ሳምንት በመራዘሙ የማነቃቂያ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ የሥልጠናው ዋነኛ ዓላማ መወዳደርና ዕድሉን ማግኘት እየቻሉ በተለያዩ ምክንያቶች ሳያመለክቱ የቀሩ ሴት መምህራንን ማበረታታትና የተሻለ የሴቶች ተሳትፎ እንዲኖር ማስቻል መሆኑን ዶ/ር ፋሲል ጠቅሰዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንትና የIUC ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ሁለተኛው ዙር የትምህርት ዕድል ውድድር ከመጀመሪያው ዙር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ቢሆንም የሴቶች ተሳትፎ ግን እጅግ አናሳ ነው ብለዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ ሴት መምህራን እናትነትና የቤተሰብ ኃላፊነት ተፅዕኖ እንዳያሳድርባቸው ከወሊድ በኋላ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ የሚችሉበት ዕድል የተመቻቸ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የባዮሎጂ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የሴት መምህራኑን ፍላጎትና ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረው መወዳደር የማያስችሉ ከባድ ሁኔታዎች ካልገጠሟቸው በስተቀር መስፈርቱን የሚያሟሉትን ሁሉ የሚጋብዝ ነው ብለዋል፡፡

በሥልጠናው የተሳተፉ ሴት መምህራን በሰጡት አስተያየት የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንና ሌሎች ጫናዎች እንዳሉባቸው ገልጸው ሥልጠናው በተያያዥ ጉዳዮች ላይ የገጠማቸውን ግራ መጋባት የቀረፈ መሆኑን እንዲሁም ለትምህርት ዕድሉ ለማመልከት እንዲወስኑ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን፣ የንዑስ ፕሮጀክት መሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት