አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ዳይሬክቶሬት ከማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እንዲሁም ከስነ ትምህርትና ስነ ባህርይ ሳይንስ እና ከሕግ ት/ቤት ጋር በመተባበር 8ኛውን ሀገር አቀፍ ምርምር ለልማት አውደ ጥናት ከግንቦት 05-06/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ 

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው ሁሉም ባለው ሙያ፣ ዕውቀትና ልምድ በጋራ በመቆምና ጠንክሮ በመሥራት ሀገራችንን ከውድቀት ልንታደጋት እንደሚገባና ይህንንም ዕውን ለማድረግ በመተባበርና በመቀናጀት በአንድ አቋም ተግባብቶ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ ዩኒቨርሲቲያችን ትክክለኛ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆነ የምንለው የመማር ማስተማር ሂደቱ በምርምር የተቃኘ፣ ምርምሩ የአካዳሚኩን ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈታ እና ለሀገር ዕድገት አስተዋፅኦ በሚያበረክት መልኩ ተከናውኖ ተግባር ላይ የሚውልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ምርምሩ ውጤታማ እንዲሆን ብቁና የተማረ የሰው ኃይል እንዲሁም በቂ ግብዓት ሊኖረን ይገባልም ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙት ት/ክፍል መምህር፣ ተመራማሪና የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ተደራዳሪ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር የጠፉ ወንዞችን፣ ምንጮችን፣ ጨፌዎችን እና የመሬት ልዩ ሀብቶችን ለመመለስ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ በ2ኛና በ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች የሚያጠኑ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብና መንግሥት በትብብር መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡   

ዶ/ር ያዕቆብ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ምሁራን ዕውቀትን ማመንጨትና የምርምር ውጤትን ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም ማሳየት የሚጠበቅባቸው ሲሆን የመንግሥት ኃላፊዎችና ፖሊሲ አስፈጻሚዎች በበኩላቸው የምሁራንን ዕውቀት ተጠቅመው በየዓመቱ እየተሻሻለና እየለማ የሚሄድ አካባቢ፣ የውሃ ሀብትና፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፈጠር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ረ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዓውደ ጥናቱ ባለፈው አንድ ዓመት የተካሄዱ የምርምር ሥራዎች ይፋ የሚሆኑበትና ለማኅበረሰቡ የሚተዋወቁበት ነው፡፡ በሚቀርቡት ምርምሮች ሳይንሳዊ ዕውቀቶች የሚፈልቁበት፣ በተለያዩ ሃሳቦች ላይ ክርክሮች የሚካሄዱበት እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ብሎም ለሀገር ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች የሚነሱበት ዓውደ ጥናት ነው ብለዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በርካታ ማኅበረሰብ ተኮር ምርምሮችን ወደ መሬት በማውረድ እየሠራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 29 ት/ቤቶችና የሕክምና ተቋማት በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉና የተለያዩ የመንገድ ሥራዎች መሠራታቸው ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ የምርምር ውጤቶችን ተግባር ላይ እንዲውሉ ከማድረግ አንጻር በቀጣይ የምርምር ግኝቶች በተሻለ ሁኔታ ወደ መሬት ወርደው ኅብረተሰቡን እንዲጠቅሙ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደገለጹት ምርምሮችን በጉድኝት ማቅረቡ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን በያዘው ዕቅድ መሠረት በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲተገብር እንዲሁም ምርምሮቹ ይዘው ከተነሱት ዓላማ አኳያ ምርምርን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የሳይንስ ዘርፉ ለሀገሪቱ ካለው የኢኮኖሚና የሰላም ማስጠበቅ ሚና ባሻገር ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢው ሁኔታ ለመጠቀም እንዲሁም የተጎዱ ቦታዎችንና ሀብቶችን እንደገና ለመሸፈንና ይህንንም በሕግ ማዕቀፍ አስደግፎ ለማስኬድ መንገድ ይጠቁማል ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ ኩሌ ኩርሻ ‹‹በአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ክልል መመሥረት የሚገኙ እድሎችና የሚጠብቁት ፈተናዎች›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ የተለያየ ባህል ያላቸው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ተዋቅረው ባሉበት በደቡብ ምዕራብ ክልል መንግሥት ለሕዝቡ የሚሰጠውን የልማት፣ የሰላም፣ አብሮ የማደግና አብሮ የመኖር ሁኔታ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ተደራሽነትን ከቀድሞው የፌዴራል ሥርዓት ጋር በማነጻጸር አሳይተዋል፡፡

‹‹Enhancing Community Development through Integrated Intervention In Malo-koza District›› በሚል ርዕስ የግራንድ ምርምር ፕሮጀክት ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የስነ ትምህርትና ስነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት መምህር ዶ/ር ቤታ ጸማቶ በመሎ ኮዛ አካባቢ ያሉ የተለያዩ የእድገት ማነቆዎችን በመቅረፍ የትምህርት ጥራትንና የሰብል ምርትን ማሻሻል፣ የእንስሳት እርባታን ማዘመን፣ መንገድ በማስከፈት ምርቶች በስፋት ለገበያ የሚቀርቡበትን ሁኔታን ማሳደግ እና የደኅንነት ስጋቶችን መቅረፍ የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከመላው የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከ50 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት