‹‹የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል የምሁራን የውይይት መድረክ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሚያዝያ 8/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የውይይት መድረኩ ከሀገራችን ተጨባጭ ችግሮች በመነሳት ወደ መፍትሔ ለመምጣት የሚያስችሉ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን ለመሰብሰብና እንደ ተቋም መሥራት ያለብንን ጉዳዮች በመቀበል ወደ ተግባር መግባትን ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል፡፡ 

ሀገራዊ ለውጡና የልሂቃን ተሳትፎ፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የመገንባት አስፈላጊነት፣ የኑሮ ውድነት የማቃለል አማራጮችን አሟጦ መጠቀም፣ ለሥራ አጥነት ችግር ትኩረት መስጠት፣ ከመንግሥታዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የተገራ የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ሥራና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች የሚሉት በውይይት ሰነዱ የተካተቱ ዐበይት ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸውን ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

በሀገር ግንባታም ሆነ በማኅበረሰብ ለውጥ ንቅናቄ ላይ የዜጎች ሚና የማይተካ በመሆኑ የልሂቃንን ተሳትፎ ማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ በውይይት ሰነዱ ተጠቅሷል፡፡ ምሁራን በታሪክ ላይ ተመሥርተው ዛሬ ላይ ሆነው ነገን ለማየት የሚችሉና የዓለምን ሁኔታ የመረዳት ደረጃቸው ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በማኅበረሰብ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚና መጫወት የልሂቃን ቀዳሚ ተግባር መሆኑን በትኩረት ያመላከተው ሰነዱ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከክርስቶስ ልደት በፊት በግሪክ፣ በሮም፣ በቻይናና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የጥንት ሥልጣኔ ባላቸው ሀገራት በስፋት የታየ ሲሆን በቅርቡም ከመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ በአውሮፓና አሜሪካ በግልጽ መታየቱን አመላክቷል፡፡

ዛሬ ላይ በኢኮኖሚም ሆነ በእርስ በእርስ መስተጋብር የተሻለ ደረጃ ላይ የምናገኛቸው ሀገሮች መነሻቸው የተቃናና የተስተካከለ ትውልድ ለመገንባት በየጊዜው የተከፈለ የዜጎችና የመንግሥት የጋራ መስዋዕትነት ውጤት ሲሆን ለሥርዓት ግንባታም የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ያልተቋረጠ ትግል ወሳኝ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ ልሂቃን የአዳዲስ ዕውቀት ማበልፀጊያ ውይይቶች፣ ክርክሮችና ተጠየቃዊ ሃሳቦችን የሚያራምዱ በመሆኑ ማንኛውንም ለውጥ ከዜጎች በተለይ ከልሂቃን ተሳትፎ ውጪ ማሳካት እንደማይቻል አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡

ከዚህም አንጻር ዩኒቨርሲቲውም ሆነ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ምሁራን ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ከመገንባት፣ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት ከማረጋገጥ፣ ለሥራ አጥነት ችግር መፍትሔ ከማመላከት፣ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጋራ ከመፍታት፣ የተገራ የሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ሥራ ከመዘርጋት አኳያና በሌሎችም ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ሳይንሳዊ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚጠበቅባቸው በውይይቱ የተመለከተ ሲሆን በውይይት ሰነዱ ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት