Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በኮሌጁ ለተመደቡ የ2ኛ ዓመት ተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል እንዲሁም በ2013 ዓ/ም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎችና ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው በአንድ ሴሚስተር የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ከየት/ክፍሉ ሁለት ሁለት ተማሪዎች የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ መርሃ ግብሩ በኮሌጁ ለ2ኛ ጊዜ መዘጋጀቱን ገልጸው ወደ ኮሌጁ የተቀላቀሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ከት/ክፍል ኃላፊዎች ጋር ለማስተዋወቅና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ለማበርከት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዲኑ ገለጻ ትውውቁ ተማሪዎቹ የሚኖራቸው የትምህርት ቆይታ የተሳለጠ እንዲሆን የሚረዳ ሲሆን የሽልማት መርሃ ግብሩም ተሸላሚዎቹን ለተሻለ ሥራ የሚያበረታታና ለተከታይ ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲተጉ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በሚኖራቸው ቆይታ ጠንካራና ተወዳዳሪ በመሆን ተቋሙን ሊያስጠሩ እንደሚገባ ዲኑ አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመዝጊያ ንግግራቸው ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ችግርና ፈተና የተጋረጠበት በመሆኑ ሰላምን ለማስፈን ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡ የአብሮነትና የመቻቻል ዕሴቶችን አዳብረው የኖሩ እናቶቻችንና አባቶቻችንን ባህል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ አክለውም ዋና ኮርስን ብቻ በመማር በቀለም ትምህርት ሙሉ መሆን ስለማይቻል በበቂ ሁኔታ ስብዕናን በመገንባት ማገናዘብ የሚችል ትውልድ ለመፍጠር እንደ ሀገር ተወስኖ የመጀመሪያ ዓመት የጋራ ኮርስ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ተማሪዎቹ በተማሩት ትምህርት ውጤታማ ሆነው ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ብሎም ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት፣ የኮሌጁ አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት