የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት (United Nations Office of the High Commissioner, East African Branch) እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ጋር በመተባበር ከዩኒቨርሲቲውና እና በከተማው ከሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለተወጣጡ 84 ተማሪዎች እንዲሁም ለመምህራንና ለዩኒቨርሲቲው ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ሠራተኞች በመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ከግንቦት 8-10/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክተው እንደገለጹት ተማሪዎች በት/ቤት ቆይታቸው መብታቸውን ማስከበርና የሌላውንም መብት ማክበር፣ ሴቶች ፆታዊ ትንኮሳ እንዳይደርስባቸው መከላከልና ከደረሰ በኋላ በሕግ መጠየቅ የሚችሉበትን መንገድ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች መብትና ተማሪዎች መከተል ያለባቸው ሥነ ምግባርን አስመልክቶ ግንዛቤ መፍጠርና አመለካከታቸውን ማሳደግ ነው፡፡ ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ በሚቋቋመው ክበብ ውስጥ አባል በመሆን ባሉበት ተቋም መብትን ከማስጠበቅ አንጻር ጠንክረው በመሥራት በተሻለ ሁኔታ የሰዎች መብት እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዲኑ አሳስበዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹የሰብዓዊ መብቶች ምንነት፣ ገደባቸውና ኃላፊነት የሚጣልባቸው አካላት›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሥልጠና የሰጡት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ምስክር ጌታቸው ሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በየትኛውም ቦታና ገደብ ከሕግ አግባብ ውጪ በማንም ሳይነጠቁና ሳይገደቡ የሚሰጡ መሆናቸውንና ይህንንም መብት መንግሥትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ባለሙያው ምስክር በአካባቢያችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ሰዎች በሕይወት የመኖርና አካላዊ ደኅንነታቸውን የመጠበቅ መብት እንዳላቸው እንዲሁም ትምህርት፣ ጤና እና ሌሎች መሠረታዊ ልማቶች ሁሉ ሊሟሉላቸው እንደሚገባ ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ከዓለም አቀፋዊ ሰነዶች አንጻር አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ክትትልና ሪፖርት አደራረግን አስመልክቶ በሥልጠናው በሰፊው ተቃኝቷል፡፡

አክለውም ተማሪዎች የሰብዓዊ መብት ግንዛቤያቸው እንዲዳብር፣ ያወቁትን ለሌላው እንዲያሳውቁና ብርታት እንዲሆኑ፣ የሰብዓዊ መብት ክበብ አባል በመሆን የክትትል ሥራ እንዲሠሩና በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ካሉ እንዲያጋልጡ፣ ውትወታና ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ማርታ ተሾመ በጾታና በሥርዓተ ጾታ መካከል ያለውን ልዩነት፣ የሴቶች መብት እንዲሁም ከሥርዓተ ጾታ ጋር በተያያዘ የሰዎች የተሳሳተ አመለካከትን አስመልክቶ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ እንደ ባለሙያዋ ገለጻ ሴቶች እንደማንኛውም የኅብረተሰብ አካል አካላቸው፣ ነፃነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ የመኖር መብት ሊያገኙ ብሎም ከአካል ጉዳት ጋር የሚኖሩ ሰዎች በሰውነታቸው የሚገባቸውን በሕገ መንግሥታችንና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውና ለሁሉም ሰው

የሚሰጡ መብቶች ሁሉ ሊከበሩላቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም የተሳሳቱ አመለካከቶች ሴቶች ሙሉ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙና የሚፈልጉትን ከመሆን እንደሚያግዷቸው ባለሙያዋ አውስተዋል፡፡

ሠልጣኖች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በሥርዓተ ጾታና በሰብዓዊ መብቶች አከባበር ዙሪያ ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን የግንዛቤ ክፍተት የሞላላቸው መሆኑንና በቀጣይም ወደየመጡበት ት/ቤትና ማኅበረሰብ በመውረድ በዘርፉ ጠንክረው በመሥራት አዎንታዊ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት