የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት የሰብዓዊ መብት ክበብ ለማቋቋምና በጋራ ለመሥራት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ጋር በየዓመቱ እየታደሰ ለ3 ዓመት የሚቆይ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ግንቦት 10/2014 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ በዕለቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴዎችም ተመርጠዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የፕሮግራም ዳይሬክተር ማህሌት አብርሃም እንደገለጹት የመግባቢያ ስምምነቱ ያስፈለገበት መሠረታዊ ዓላማ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ክበብ በማቋቋም ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ ተማሪዎች ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ያላቸውን አቅም በማጎልበት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና ከራሳቸው አልፈው ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥሩበትን እንዲሁም ስለ ሰብዓዊ መብት የሚከራከሩበትና እርስ በእርስ የሚማማሩበት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ በተጨማሪም ሰነዱ ላይ በሰፈረው ስምምነት መሠረት ሥራዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ክበቡ የሚቋቋምበት ዓላማ እንዲሁም ከተቋቋመ በኋላ እንዲጠናከር ሥልጠና፣ ልምድ ልውውጥና ክርክሮችን እንዲያዘጋጁ የተለያዩ ድጋፎችና የአፈጻጸም ውጤቶችን መከታተል የማዕከሉ ኃላፊነቶች መሆናቸው ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል የሕግ ት/ቤት ክበቡን መመሥረት፣ የክበቡን ሥራዎች የሚከታተልና የሚቆጣጠር የራሱ ተጠሪ እንዲኖረው ማድረግ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከማስቆም አንጻር በአግባቡ እየሠሩ መሆኑንና ያከናወኗቸውን ተግባራት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ክትትል ማድረግ እና ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ፈንድ የማፈላለግ ሥራ መሥራት እንዳለበት በመግባቢያ ሰነዱ ተካቷል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ለ1 ዓመት የሚሠራና በየዓመቱ እየታደሰ ለ3 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ሥራዎች በንቃትና በተቀላጠፈ ሁኔታ ካልተከናወኑ ስምምነቱ ሊፈርስ እንደሚችል በሰነዱ ተጠቁሟል፡፡ የተመረጡት ኮሚቴዎች ከሥልጠናው በኋላ ክበቡን ይመሠርታሉ፣ አባላትን ይመዘግባሉ፣ ከአባላቱ ጋር በመሆን የሰብዓዊ መብት ቀን እንዲከበር የተለያዩ ፕሮግራሞችን ያዘጋጃሉ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ሃሳብ መስጠት፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት፣ ክርክሮችን፣ ውይይቶችንና የችሎት ውድድሮችን ማዕከሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለአባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀትና የሠለጠኑትን ሥልጠና ለአባላት መስጠት የኮሚቴው ሥራ መሆኑ በሰነዱ ተጠቁሟል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ሠልጣኞች በወሰዳችሁት ሥልጠና መሠረት አዳዲስ ሃሳቦችን ለማፍለቅና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የበኩላችሁን አስተዋጽኦ በትጋት ማበርከት ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ክበቡ ከሌሎች መሰል የፍትሕ አካላት ጋር በመተባበር አርአያ ሆኖ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው የክበቡ አባላት በሚገባ ተጠናክረው ክበቡን ለተሻለ ደረጃ እንደሚያበቁትና በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሌሎች ት/ቤቶች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና በተለይም የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት