Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት በሁሉም ካምፓስ በሚገኙ የቅድመ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች የግለ ግምገማ ሰነድ አዘገጃጀት ዙሪያ ግንቦት 10/2014 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት እንደ ሀገር እየተሰጠ ያለው ትምህርት የሚፈለገውን ያህል ግብ እንዲመታ ለማስቻል በሀገር፣ በዩኒቨርሲቲ፣ በኮሌጅና በትምህርት ክፍል ደረጃ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የግለ ግምገማ ሰነድ ለማዘጋጀት እንደ መነሻ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና የውጭ ተሞክሮ ባላቸው መምህራን ስለፕሮግራም ኦዲት፣ አክሪዲቴሽን(Accreditation)ና ስታንዳርዳይዜሽን (Standardization) ሥልጠና መስጠቱን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዶ/ር ዓለማየሁ ሥልጠናውን መነሻ በማድረግ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተወዳድረን ለመውጣትና የትምህርት ፕሮግራሞቻችን የሀገር ውስጥና የውጭ ዕውቅና እንዲያገኙ፣ ተማሪዎቻችንና መምህራኖቻችን በተመቻቸና በተሟላ መልኩ የማማር ማስተማር ተግባር እንዲያከናውኑ ለማስቻል ሰነዱ መዘጋጀት አለበት ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ በውጭ አካላት አክሪዲቴሽን(Accreditation) ከማሠራታችን በፊት የውስጥ ግምገማ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ በከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን ፎርማት እንደ መነሻ በመጠቀም የትምህርት ፕሮግራሞቻችንን ግምገማ ብናደርግና ከግምገማው ከሚገኘው ውጤት ተነስተን መሥራት ብንጀምር አሁን ባለንበት ሁኔታ ለማስተካከል ብዙ ርቀት ያስኬደናል፡፡ ከዚህ አንጻር መማር ማስተማር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ቤተ-ሙከራ፣ ወርክ ሾፕ፣ ቤተ-መጻሕፍትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ያሉበትን ደረጃ በጥልቀት በመመልከት የፕሮግራሞቹ ግለ ግምገማ ሰነድ እንዲዘጋጅ አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምግምና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ እንደተናገሩት ግለ ግምገማው በሁሉም ካምፓስ በሚገኙ 76 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች የሚካሄድ ሲሆን ዓላማውም እንደ ሀገር የተያዘውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማምጣት፣ በትምህርት ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ለቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን እያሻሻሉ መሄድና በትምህርት ፕሮግራሞቻችን ዙሪያ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘት ነው፡፡ በቀጣይም ግለ ግምገማው በ114 የ2ኛና በ26 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ይካሄዳል ያሉት ዶ/ር ሠረቀብርሃን ይህም ኮሌጆቻችንና ትምህርት ክፍሎቻችን ከተለያዩ አደረጃጀቶች አንጻር ምን እንደሚመስሉና የሚጎድላቸውን ነገር ለመለየት ይጠቅመናል ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ዋና ዓላማ እንደ ትምህርት ተቋም የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ነው ያሉት የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን የትምህርት ፕሮግራሞቻችንን በመገምገምና ችግሮቻችንን በመለየት መሻሻል ያለባቸውን እያሻሻልንና እያስተካከልን መሄድ ከቻልን ዘመኑ የሚፈልገውን የትምህርት ጥራት ማምጣት እንችላለን ብለዋል፡፡

የሲቪል ምኅንድስና ፋከልቲ ኃላፊና የሲቪል ምኅንድስና ትምህርት ፕሮግራሞች ግለ ግምገማ ሰነድ አዘጋጆች ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ መለሰ ሥልጠናው የግለ ግምገማ ሰነድ ምንነት፣ አዘገጃጀት፣ መካተት የሚገባቸው ይዘቶችና የኮሚቴዎች አወቃቀርን አስመልክቶ በዝርዝር ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ፣ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለና የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁንን ጨምሮ በሁሉም ካምፓስ የሚገኙ የቅድመ ምረቃ ት/ክፍል ኃላፊዎችና ነባር መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት