የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የ3ኛ ዲግሪ ምሩቃን በ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራም መማር ለሚፈልጉ በትምህርት ሂደቱ ዙሪያ ግንቦት 10/2014 ዓ/ም የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል፡፡ 

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ እንደገለጹት በኮሌጁ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር አናሳ በመሆኑና በትምህርት ዕድል ውድድር ላይ የመምህራን ተሳትፎ ዝቅተኛ በመሆኑ የልምድ ልውውጡ ችግሩን ለመቅረፍና የምሁራኑን ቁጥር ለመጨመር መምህራንን ለማነሳሳትና ለመደገፍ ያለመ ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በ3ኛ ዲግሪ የተማሩ መምህራንን ከየትምህርት ክፍሉ በመጋበዝ ያለፉበትን መልካም አጋጣሚዎችና የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች በማቅረብ ልምድ እንዲያካፍሉ መደረጉን ዶ/ር መስፍን ተናግረዋል፡፡ 3ኛ ዲግሪ ያላቸውን መምህራን ቁጥር ማሳደግ ተቋሙ እንደ ምርምር ተቋም በርካታ የምርምር ሥራዎችን እንዲሠራ ከማገዙም በላይ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለኮሌጁ፣ ለዩኒቨርሲቲው ብሎም ለሀገር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኮሌጁ ም/ዲን አቶ አወል በክር ኮሌጁ ወጣት መምህራን ያሉበት ቢሆንም የ3ኛ ዲግሪ ምሩቃን ቁጥር አናሳ በመሆኑ መምህራኑን በትምህርት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በ3ኛ ዲግሪ ለመማር ያለውን ሂደት በግልጽ እንዲረዱና ለሚገጥማቸው ሁሉ ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ የልምድ ልውውጥ መድረኩ ተዘጋጅቷል፡፡

በ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ላይ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የመመረቂያ ጽሑፍ ማዘጋጀት መሆኑን የገለጹት የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምር ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር ተክለብርሃን ዓለምነህ የመመረቂያ ጽሑፍ ርዕስ አመራረጥ፣ የጥናት ንድፍ አዘገጃጀት፣ ጥናታዊ ጽሑፍን ማሳተምና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት