የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‹‹ስነ-ቃል ለሀገራዊ መግባባት›› በሚል ርዕስ ግንቦት 13/2014 ዓ/ም ሀገራዊ ሲምፖዚየም አካሂዷል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው ስነ-ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል የሚሸጋገር እንዲሁም በቁጥብ ቃላት ረቂቅና ሰፊ መልዕክት የሚተላለፍበት መሆኑን ገልጸው ሀገራችን ኢትዮጵያ በበርካታ ሰው ሰራሽ ችግሮች ተተብትባ ባለችበት በዚህ ወቅት የስነ-ቃልን ጥበባዊ ጉልበት ለማኅበረሰብ መግባቢያነት ብንጠቀመው ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ መሰል መድረኮች ከመማማሪያነት ባሻገር ለወደ ፊት የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዱም ተናግረዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ በሺዎች የሚቆጠሩ ትርክቶችና አባባሎች ባለቤት መሆኑን ገልጸው ስነ-ቃሎቹ በተለያዩ ጊዜያት ለሥነ-ምግባር፣ ለግጭት አፈታትና ለሀገር ግንባታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በገጠራማው የሀገራችን ክፍል ካልሆነ በስተቀር ከተማ ላይ ስነ-ቃል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየጠፋ በመሆኑ በተለያዩ ቋንቋዎች ምርምሮች አየተሠሩና እየተተነተኑ ተሰንደው ለመጪው ትውልድ መተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ስነ-ቃል ለሐዘን፣ ለደስታ፣ ለይቅርታ፣ ለጦርነት ዝግጅት፣ ለሕዝብ ግንኙነት እና ለመሳሰሉት ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የምንጠቀምበት እሴታችን ሲሆን ለሀገራዊ መግባባት እንዲጠቅም አድርጎ ከመሥራት አንፃር ግን ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ስነ-ቃል ለሀገራዊ መግባባት እንዲጠቅም በየዘርፉ በተለያየ ቋንቋ ተሰብስበውና በባለሙያዎች ተሰንደው በሥርዓተ ትምህርት፣ በማኅበረሰብ ውይይትና በተለያዩ ኮንፍረንሶች እየቀረቡና እየተተነተኑ ለሀገር ሰላም ግንባታ እንዲውሉ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ቋንቋ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው እንደተናገሩት የኅብረተሰቡ የማንነት መገለጫ የሆነውን ስነ-ቃል ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎች እና መንግሥት ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሀገር በቀል ምርምሮችን ከማበረታታት አንጻር ሲምፖዚየሙ ከፍተኛ ሚና አለውም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አህመድ እንደገለጹት ሲምፖዚየሙ ዩኒቨርሲቲው ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን ከማዳረስ አንጻር ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ ሲሆን ሀገራችን የጀመረችውን ሀገራዊ መግባባት ለማገዝ የሚረዳ ነው፡፡ ሲምፖዚየሙ በየዓመቱ በሀገረሰባዊ ዕውቀቶች ላይ ሲዘጋጅ 6ኛው ሲሆን በዚህ ዓመት ስነ-ቃልን ብቻ በማተኮር ተዘጋጅቷል፡፡ በቀጣይም እንደ ተቋም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ዶ/ር ሰኢድ ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የፎክሎርና ስነ-ጽሑፍ መምህር የሆኑት ዶ/ር ተመስገን ምንዋጋው ‹‹የየት መጣ ሚት የጋሞ አብሮነት አምድ ሲሆን›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡ ሲሆን የጽሑፉ ዓላማ ስነ-ቃል ለሀገራዊ መግባባት ያለውን ፋይዳ ማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተመስገን በጥናታዊ ጽሑፋቸው በጋሞ ውስጥ ከሚታወቅ ሚት(Myth) ተነስተው የጋሞ ብሔረሰብ አመጣጥና አንድነት፣ የችግር አፈታት ስልት፣ ሰላማዊ የእርስ በእርስ ግንኙነት የተመሠረተበት መንገድና በሂደቱም ላይ የዋለው የግጭት አፈታት እስከ አሁንም ድረስ በሥራ ላይ መኖሩና ተሞክሮውን ሀገራዊ ስለማድረግ አስፈላጊነት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ዶ/ር ተመስገን በማጠቃለያቸው ስነ-ቃል ሀገርን የማልማትም ሆነ የማጥፋት ኃይል እንዳለው ጠቅሰው ያለንን ስነ-ቃል በመጠቀም ከገባንበት ችግር የመውጣት እድላችን ሰፊ ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛዋ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህርት እና የዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አስቴር ሙሉ ‹‹በአማርኛ ቋንቋ የሚነገሩ ምሳሌያዊ ንግግሮች ሰላምን የመገንባት ፋይዳ በባሕር ዳርና አካባቢው ተተኳሪነት›› የሚል ርዕስ ያለው ነው፡፡ እንደ ዶ/ር አስቴር ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ላጋጠማት የሰላም እጦት ከዚህ በፊት ሲነገሩ የነበሩና ለዘመናት አብረውን የመጡ የሐሰት ትርክቶች ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ስነ-ቃሎች ሰላምን የመገንባት ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ ሀገር በህልውናዋ እንድትቀጥል የስነ-ቃል ሀብትን በመሰብሰብና በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት የሐሰት ትርክቶቹን የመሻር ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ 14 ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና የሰላም ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካዮች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የተለያዩ ክልሎች የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የኦሮሚያ ክልል ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከጋሞ ዞን ወረዳዎችና ከአርባ ምንጭ ከተማ የተጋበዙ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት፣ መምህራንና ተማሪዎች በሲምፖዚየሙ ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት