Print

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሙያ መመሪያ እና የምክር ማዕከል (Career Guidance and Counseling Center) ደረጃ ዶት ኮም ኃ.የተ.የግ. ድርጅት /Dereja.Com/ እና አይ - ጆብ ሪክሪዩትመንት (I-Job Recruitment) ከሚባል የግል ድርጅት ጋር በመተባበር ለ2014 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች ከግንቦት 05-13/2014 ዓ/ም የሥራ ዝግጁነት /Job Readiness/ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማዕከሉ አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ እንደገለጹት የ2014 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ተቋሙ የትምህርት ጊዜያቸውን አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊት ወደ ሥራ ዓለም ለመግባት የሚረዷቸውን እና ተወዳዳሪና ብቁ የሚያደርጓቸውን ክሂሎቶች እንዲያገኙ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ ሥልጠናው የሥራ መመሪያና ምክክር ሳምንት /Career Guidance and Counseling Week/ ውስጥ የሚሰጥ ሲሆን ዓላማውም ለተመራቂ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃና ካሪኩለም ቪቴ/CV/ ዝግጅት፣ ለሥራ ቃለ-መጠይቅ ዝግጅት እና በሥራ ቃለ መጠይቅ ወቅት ራስን ለቀጣሪ መሥሪያ ቤት የመግለጽ ክሂሎት ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡

ሥልጠናው አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ከሚማሩበት ተቋም ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት ብቁ ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርጓቸውን አስፈላጊ ክሂሎቶች በማግኘትና ራሳቸውን ብቁ ባለሙያ በማድረግ በሚወዳደሩበት ቦታ ሁሉ ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

ከአይ - ጆብ ሪክሪዩትመንት (I-Job Recruitment) ድርጅት ልምዳቸውን ያካፈሉት አቶ አምሳሉ ሁሉቃ እንደተናገሩት ጆብ ፌር/Job Fair/ ሥራውን በአርባ ምንጭ ከተማ ከጀመረ 2 ዓመት ያለፈው ሲሆን በሀገራችን በተማረው የሰው ኃይል ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ቴክኒካዊ ክሂሎቶች ዙሪያ አጫጭር ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ትኩረታቸውን በትምህርትና ውጤት በመሰብሰብ ላይ አድርገው የቆዩ በመሆኑ ለሥራ ቅጥርና ለቃለ መጠይቅ የሚያስፈልግ ዝግጅት እንዲሁም ከአዲስ ተቀጣሪዎችና ከቀጣሪ ድርጅቶች እንደ ችግር በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ልምዳቸውን ማካፈላቸውን ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ጥናት መምህር የሆኑት አሠልጣኝ ዘርይሁን ኃይሉ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡ የሚጠብቃቸው የሥራ ዓይነት፣ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ጋር ያሉ የሥራ አማራጮችና እንዴት ለሥራ መዘጋጀት እንዳለባቸው አሠልጥነዋል፡፡ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር ለውጠው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ የሚረዳ ሥልጠና መሆኑን አሠልጣኙ ተናረዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በመዝጊያ ንግግራቸው እንደገለጹት በትምህርት የተገኘ ዕውቀት በአቀራረብና አገላለጽ ሁኔታ ሊሸፈን የሚችል በመሆኑ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የሰውኛ ክሂሎቶች/Soft Skill/ሥልጠና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ምርምሮችና የሥራ ማመልከቻዎች በአግባቡ መያዝና አንባቢውን በሚስብ መልኩ መቅረብ ይገባቸዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ሠልጣኞች ያገኙትን ክሂሎት በCV ዝግጅት፣ በሥራ ማመልከቻ፣ በሥራ ቃለ መጠይቅና ሌሎችም አስፈላጊ ቦታዎች እንዲጠቀሙበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊ የሆነችው በዩኒቨርሲቲው የ5ኛ ዓመት የኤሌክትሪካል ምኅንድስና ተማሪ አቅሊሲያ አታክልት ተማሪዎች ከትምህርት ዓለም ከወጡ በኋላ በሥራ ፍለጋ ወቅት ለሚገጥማቸው ችግር ብቁ ሆነው እንዲገኙ ሥልጠናው ክሂሎት የሚያስጨብጥ መሆኑን ተናግራ ለሥራ ፍለጋና ቅጥር እንዴት መዘጋጀት እንዳለብኝ አስገንዝቦኛል ብላለች፡፡

ሥልጠናው በመጀመሪያ ሳምንት በዋናው ግቢ፣ በዓባያና በጫሞ ካምፓሶች የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም በሌሎች ካምፓሶች ያሉ ተመራቂ ተማሪዎችን በማሠልጠን የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት