ከታኅሣሥ 08/2014 ዓ/ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ግንቦት 14/2014 ዓ/ም አፈ-ጉባኤና ም/አፈ-ጉባኤ በመምረጥ ተጠናቋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ ምርጫው ረዥም ጊዜ መውሰዱንና ፍትሐዊ፣ ግልጽና ተአማኒ በሆነ መንገድ መከናወኑን ገልጸው ይህን ሂደት አልፎ የመጣው ፓርላማ የተማሪውን ጥያቄዎች ለመመለስ ተግቶ እንደሚሠራ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የሲቪክስ ተማሪና የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ አዲሱ ተመራጭ አፈ-ጉባኤ ተማሪ መልካሙ ዓለምነህ ስለ ምርጫው ሲናገር በማስታወቂያው መሠረት ከተመዘገቡ 8 ተማሪዎች መካከል 5ቱ ለቃለ-መጠይቅ መቅረባቸውን ጠቅሶ ለጠቅላላው ፓርላማ ከቀረቡ 3 ተማሪዎች መካከል ለአፈ-ጉባኤነት አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ እንዳስተሰተው ተናግሯል፡፡ በመመሪያው መሠረት ከብሔር፣ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ለማገልገልም ቃል ገብቷል፡፡

የ5ኛ ዓመት የሶፍትዌር ምኅንድስና ተማሪና የ2014 ዓ/ም የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተማሪ አንሙት ጎዴ በበኩሉ በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ የጊዜ ሰሌዳ በተለያዩ ምክንያቶች መራዘሙን ገልጾ በምርጫው ከብሔርና ጾታ ተዋፅኦ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች በመመሪያው መሠረት አሳማኝ ምላሾች መሰጠታቸውን ተናግሯል፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታን ጨምሮ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴና የአዲሱ ፓርላማ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት