Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ለጫሞ ካምፓስ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች አቀባበልና የላቀ ውጤት ላመጡ የ3ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች የሽልማት መርሃ ግብር ግንቦት 11/2014 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ 

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ ለአዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ትኩረታቸውን ለትምህርታቸው በማዋል የላቀ ውጤት ለማስመዝገብና የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በጥንካሬ ለማለፍ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ነባር ሴት ተማሪዎች ከሚያካፍሉት የሕይወት ተሞክሮ ልምድ በመቅሰምና በተግባር በማዋል ለውጤት መብቃት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ካምፓሱ ከሚታወቅባቸው አኩሪ ተግባራት አንዱ የሆነው የሴት መምህራን ኔትወርክ ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመወያየት የሚፈታና ሌሎችም ተግባሮችን የሚያከናውን መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ተማሪዎቹ በተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸውና የሚገጥሟቸውን ችግሮች በቅርበት ለዳይሬክቶሬቱ በማማከር መፍትሄ ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉም ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ አክለውም ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ለትምህርታቸው ቅድሚያ በመስጠትና ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት፣ ክሂሎትና የተለያዩ የማኅበራዊ ሕይወት ልምዶችን አዳብረው ራዕያቸውን ለማሳካት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የቀድሞ የካምፓሱ ተማሪዎች የነበሩ መምህራንና የ3ኛ ዓመት ተሸላሚ ተማሪዎች የሕይወት ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሳይንስ ኮሌጅ እና የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲኖች፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ባለሙያዎች፣ የዜሮ ፕላን ተወካይ እና የሴት መምህራን ኔትዎርክ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት