አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Christian Aid››/ክርስቲያን ኤይድ/ ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር የእንሰት አመራረትና ማብላላት ሂደትን ለማዘመን የሚረዱ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ 3.2 ሚሊየን ብር የተመደበለት ፕሮጀክት በትብብር እየሠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የፕሮጀክቱን የሥራ እንቅስቃሴና አፈፃፀም አስመልክቶ ከድርጅቱ የመጣ ቡድን ግንቦት 16/2014 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ምልከታ አድርጓል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ከክርስቲያን ኤይድ ጋር በትብብር መሥራታችን ፋይዳው ሀገራዊ መሆኑን ተናግረው የትብብር ሥራው ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ዙሪያ ያሉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የጀመረውን የተግባር እንቅስቃሴ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ዙሪያ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት፣ አዳዲስ የምርምር ውጤቶችና ግኝቶች አሁን ላይ ከሀገር አልፈው ዓለም አቀፍ ትኩረት እያገኙ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ የእንሰት ጉዳይ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት በፖሊሲ እንዲካተት ዩኒቨርሲቲው እየሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከድርጅቱ ጋር የጀመረው የትብብር ፕሮጀክት እንዲሳካና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡    ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ የእንሰት አመራረትና ማብላላት ሂደትን የሚያዘምኑና የሚያሻሽሉ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በማምረት ለማኅበረሰቡ ለማዳረስ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክርስቲያን ኤይድ የተሰኘው ድርጅትም ከእንሰት ጋር በተያያዙና በሌሎች መስኮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ በኦንላይን ተፈራርሟል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎቹን በስፋት አምርቶ ለድርጅቱ በማቅረብ ለአርሶ አደሩ እና በሥራ ፈጠራና ቢዝነስ ዘርፎች ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ተደራሽ እንዲደረግ ድርጅቱ 3.2 ሚሊየን ብር በጀት መመደቡን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በበኩላቸው ከድርጅቱ ለመጀመሪያ ዙር በተመደበው 1.6 ሚሊየን ብር የሀምቾ መቁረጫ፣ የሀምቾ መፍጫ፣ የቡላ መጭመቂያ፣ ቆጮን ከቃጫ መለያ ማሽኖች እንዲሁም ከሴራሚክና ከፕላስቲክ የተሠሩ የቆጮ ማብላያዎችና የማብላላት ሂደትን የሚያፋጥኑ እርሾዎች በስፋት እየተመረቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በእስከ አሁኑ ሂደት በ5 ወራት ውስጥ የሥራው 30 በመቶ መጠናቀቅ መቻሉን የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ ሥራውን ከስምምነቱ ቀን ቀደም ብሎ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ከድርጅቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክርና በቀጣይ መሰል የትብብር ፕሮጀክቶችንም ለማግኘት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

በክርስቲያን ኤይድ ፕሮግራም የገበያና ኢንተርፕራይዝ ልማት እንዲሁም የአኗኗር መሻሻል ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ተካልኝ ከበደ ድርጅታቸው ከአውሮፓ ሕብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በወላይታ ዞን እንሰት አብቃይ ሁለት ወረዳዎች ኋላ ቀር የሆነውን የእንሰት አመራረትና ማብላላት ሂደት በማሻሻል አርሶ አደሩ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጾ

በሚንቀሳቀስበት ወቅት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመስኩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥሮ እየሠራ መሆኑን በመገንዘብ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡ በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂዎቹን በስፋት በማምረት የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን የተናገሩት አቶ ተካልኝ በዚህም መሠረት የዩኒቨርሲቲው የሥራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ለመጎብኘትና ለመገምገም እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጉብኝታቸውም የዩኒቨርሲቲው የሥራ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን እንደታዘቡና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለስርጭት የተዘጋጁ ቴክኖሎጂዎች ከጠበቁት በላይ ሆነው ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተጀመረውን የትብብር ሥራ በእንሰትም ሆነ ሌሎች ዘርፎች የማኅበረሰቡን ሕይወት የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እንደሚቀጥሉ አቶ ተካልኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹Christian Aid››/ክርስቲያን ኤይድ/ ዋና መሥሪያ ቤቱን እንግሊዝ ሀገር አድርጎ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍ፣ የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት የኅብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ በማሻሻል እና ሰብዓዊ እርዳታዎችን በማድረስ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት