Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አስተባባሪነት በማሕፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ነጋ ጩፋሞ የተመራ የሕክምና ቡድን በገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በመገኘት ለ4 አቅመ ደካማ እናቶች ነፃ የማሕፀን ውልቃት/መንሸራተት ቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት ግንቦት 19/2014 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር የሆኑት የማሕፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ነጋ ጩፋሞ ማሕፀን በእርግዝና ጊዜ ልጅ የሚያቅፈው የሴቶች መራቢያ አካል ሲሆን ማሕፀን የተፈጥሮ ቦታውን ለቆ ወደ ታች በመንሸራተት በብልት ጫፍ ላይ ሲመጣ ወይም ሙሉ በሙሉ ከብልት ሲወጣ የማሕፀን ውልቃት/መንሸራተት ተከሰተ እንደሚባል ተናግረዋል፡፡ ይህ ችግር የሚፈጠርባቸው እናቶች ብዙ ልጆችን አምጠው የወለዱ፣ ከባድ ዕቃ የሚሸከሙ ወይም ረጅም መንገድ በእግር የሚጓዙ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ነጋ በአብዛኛው እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ እናቶች የችግሩ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

የማሕፀን ውልቃት የገጠማቸው እናቶች ለበርካታ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች እንደሚጋለጡ የተናገሩት ስፔሻሊስቱ ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል፣ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት፣ የሽንት ኢንፌክሽን መከሰት፣ የሽንት እምቢ ማለት ወይም መሽናት አለመቻል፣ የብልት ቁስለት፣ የጀርባ ህመምና የመሳሰሉ የጤና እክሎችም ሊከሰቱ ይችለሉ ብለዋል፡፡


እንደ ዶ/ር ነጋ በኮሌጁ ማኅበበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪነት በተለይ አቅመ ደካማ እናቶችን በመለየት በሆስፒታሉ በተለያዩ ጊዜያት ነፃ የሕክምና አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን በየዙሩ ከ3-5 እናቶችን ማከም ተችሏል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በየተማረበት መስክ ማኅበረሰብን ሊያገለግል ይገባል ያሉት ዶ/ር ነጋ በተለይ አቅመ ደካማ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማገልገል ከምንም በላይ ትልቅ ደስታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በግላቸው መሰል አገልግሎቶችን በሌሎች የገጠር ሆስፒታሎችም ጭምር ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ነጋ ሁሉም ባለሙያዎች በመሰል ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ተ/ፕ ወይንእሸት ገ/ፃዲቅ በበኩላቸው ኮሌጁ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በኮሌጁ የሚገኙ የጤናና ሕክምና ባለሙያዎችን በመጠቀም በተለያዩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በመገኘት ሙያዊ ድጋፎችን እንደሚሰጥ አስታውሰው ከድጋፎቹ መካከል በገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በዚህ ዓመት ለ4 ዙሮች የተሰጠው የማሕፀን ውልቃት ቀዶ ጥገና አገልግሎት ይገኝበታል ብለዋል፡፡ በከምባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልም ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርቡ አገልግሎቱ መሰጠቱን የገለጹት ዳይሬክተሯ በቀጣይ በሌሎችም የሕክምና ዘርፎች ነፃ የቀዶ ጥገና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


የገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ወርቁ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዜያት ለሆስፒታሉ የሕክምና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በተለይ በማሕፀን ውልቃት ላይ በቋሚነት እየተሰጠ ያለው ነፃ የሕክምና አገልግሎት በርካታ አቅመ ደካማ እናቶችን ከስቃይ የታደገና ሕክምናውን ለማግኘት ሲባል ወደ ሌሎች ከተሞች መሄጃ ገንዘብንና እንግልትን እንዲሁም የጊዜ ብክነት የሚያስቀር ነውም ብለዋል፡፡

ከመሰል ሙያዊ ድጋፎች ባሻገር በሆስፒታሉ ለሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት የሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥና የደንበኞች እርካታ ከፍ እንዲል ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እስከ ዛሬ ላደረገውና እያደረገም ላለው ድጋፍ በሆስፒታሉና በተጠቃሚ ማኅበረሰብ ስም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለወደ ፊቱም መሰል ድጋፎችን በሌሎችም የሕክምና ዘርፎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡