Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት በ2013 እና 2014 በጀት ዓመታት ወደ መኅበረሰብ ወርደው ትግበራ ላይ የሚገኙ የምርምር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማ ግንቦት 30/2014 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዩኒቨርሲቲው ከማኅበረሰብ ጉድኝት አኳያ በየዓመቱ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ግምገማው በ2013 እና 2014 በጀት ዓመታት ፀድቀው ወደ መኅበረሰብ ወርደው ትግበራ ላይ የሚገኙ ምርምርን መሠረት ያደረጉ የማኅበረሰብ ጉድኝት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም የሚገመግም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ከሚነሱ ጠንካራ ጎኖች ልምድ የሚቀሰምበትና በተግዳሮቶች ላይ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንዲሁም ለቀጣይ ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመቅረጽ የሃሳብ ግብዓት የሚሰበሰብበት ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገር ዕድገት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልፀው ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጥናታዊ ጽሑፎች እየተሠሩ ከኅትመት ባሻገር ወደ ተግባር ተቀይረው በቀጥታ የማኅበረሰቡን ሕይወት ሊቀይሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶች መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ የዚህ ዓይነቱ አሠራር ማኅበረሰቡን በተሻለ ደረጃ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ከማድረጉም በላይ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን የማኅበረሰብ ጉድኝት አገልግሎት ለሰፊው ማኅበረሰብ ተደራሽ እንዲያደርግ ያስችላል፡፡

የምርምርና ማኅ/አገ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ መርሃ-ግብሩ በዓይነቱ የመጀመሪያ ሲሆን የምርምር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የሚገመገምበት እንደሆነ ገልፀው የበለጠ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ፕሮጀክቶች እንዴት ሊሠሩ እንደሚችሉ የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ነው ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ግምገማ ማኅበረሰቡን ትኩረት ያደረገ እንደመሆኑ በማኅበረሰቡና ዩኒቨርሲቲው ትስስር ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

ምክትል ፕሬዝደንቱ ለአብነት የባዮ ጋዝ አጠቃቀም ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን የጠቀሱ ሲሆን ይህም ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በትብብር በምዕራብ ዓባያ፣ ቦንኬ፣ ገረሴ እና አ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተሠሩ የባዮ ጋዝ ማብላያ ግንባታዎች ለአካባቢው ኅብረተሰብ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም እነዚህን የመሳሰሉ ቤተሰብ ተኮር የሆኑ ትርፋማ ፕሮጀክቶችን የማስፋት ዕቅድ መኖሩንና የአፈጻጸም ግምገማው የበጀት አጠቃቀምንም ያካተተ መሆኑን ተ/ፕ በኃይሉ ጠቁመዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት ምርምርን መሠረት ያደረጉ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ከ4 ዓመታት በፊት የተጀመሩ ሲሆን መርሃ-ግብሩ ባለፉት ጊዜያት በተለይ በ2013 እና 2014 በጀት ዓመታት ውስጥ የተሠሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የሚገመገምበት ነው፡፡ ዳይሬክተሩ በምርምር ላይ መሠረት ያደረጉ 4 ዓይነት ማለትም ዓመታዊ፣ ግራንድ፣ የጋራ እና የትብብር ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልፀው ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት መደበኛ በጀት ብቻ ሊሠሩ የማይችሉና የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የማኅበረሰቡን ጉድኝት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በ2014 ዓ/ም ወደ ትግበራ ከወረዱ ግራንድ ፕሮጀክቶች አንዱ ከፍተኛ በጀት ተመድቦበት በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ላይ እየተሠራ የሚገኘው የእንሰት ምርታማነት፣ ማብለያና እሴት የተጨመረባቸው የእንሰት ምግቦች አዘገጃጀት ላይ የሚያተኩረው የእንሰት ፕሮጀክት መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

“Preparation and Entrepreneurship Training on Medicated Soap Making Operation Using Easily Accessible Row Material” የሚለውን የምርምር ፕሮጀክት አፈጻጸም ያቀረቡት የኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህር ረ/ፕሮፌሰር ነብዩ ጫሊ እንደገለጹት 17 በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ማኅበራት ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በቀጣይም አራት የተለያዩ ማኅበራትን ለማሠልጠን በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

የአፈር መሸርሸር እና መደርመስ፣ ዘመናዊ የንብ እርባታ፣ የባዮ ጋዝ አጠቃቀም፣ የጋሞኛ ቋንቋ መማሪያ መተግበርያ፣ የልደት ምዝገባ ግንዛቤ ማሳደግ፣ የደም ግፊት ምርመራ እና ራስን መንከባከብ፣ የሽመና ምርቶችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ፣ ቀርከሃን መሠረት ያደረገ የመተዳደሪያ ዘዴ መጠቀምና የመሳሰሉት በመርሃ-ግብሩ ቀርበው ከተገመገሙ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በግምገማው የ37 ምርምር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የቀረበ ሲሆን የሚመለከታቸው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮችና አስተባባሪዎች እንዲሁም ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት