Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ከሰኔ 4-5/2014 ዓ/ም በአዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል የእግር ኳስ ውድድር ተካሂዷል፡፡

የስፖርት አካዳሚ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ከተማ በውድድሩ መክፈቻ እንደተናገሩት አካዳሚው በዕቅድ ይዞ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል በት/ክፍሎች መካከል ስፖርታዊ ውድድሮችን ማካሄድ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ዓመት ከ60 በላይ ውድድሮችን አካሂደናል ብለዋል፡፡ ስፖርታዊ ውድድሮች ጤናን ለመጠበቅ፣ አእምሮን ለትምህርት አቀባበል ዝግጁ ለማድረግ፣ የእርስ በእርስ ትውውቅ ለመፍጠርና አካባቢን በቀላሉ ለመልመድ ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት አቶ አሰግድ ውድድሩ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ስፖርት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ዋንታሼ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ከምርምር ባሻገር በስፖርቱ ዘርፍ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማሳየትና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች በሚፈልጉት የስፖርት ዘርፍ እንዲሳተፉ ግንዛቤ ለመስጠት ጭምር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ውድድሩ በኩልፎ፣ ነጭ ሳር፣ ዓባያና ጫሞ ካምፖሶች ወንድ ተማሪዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ካምፓሶች ሴቶችንም በማሳተፍ በእግር ኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በቅርጫት ኳስና በሜዳ ቴኒስ ስፖርቶችን ለማካሄድ ዕቅድ መያዛቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓባያ ካምፖስ የ‹‹ሰላም እግር ኳስ ቡድን›› መሪ ተማሪ ዳዊት ሸለሜ በአቀባበሉም ሆነ በውድድሩ ደስ መሰኘቱን አስተያየት ሰጥቷል፡፡ የ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› ቡድን መሪ ተማሪ ይዲዲያ ትንሣኤ በበኩሉ አርባ ምንጭ ከተማ ከልምላሜዋ በተጨማሪ በስፖርቱ ዘርፍም ስሟ የሚጠራ መሆኑን አስታውሶ ይህንንም በተደረገልን ስፖርታዊ አቀባበል አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ በስፖርታዊ ውድድሮች ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ተማሪዎች ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም ገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት