Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በሥራ ላይ ልምምድ የቆዩ የኮሌጁ መምህራንን ሪፖርት ሰኔ 04/2014 ዓ/ም ገምግሟል፡፡ በዕለቱ ከመንግሥትና ከግል ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችል የስምምነት መግባቢያ ሰነድም ተፈራርሟል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ የሥራ ላይ ልምድ ልውውጥ ግምገማ ልምዶች፣ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ለመምከር እና ወደ ፊት የተሳካ ትስስር ፈጥሮ የበቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን በኢንደስትሪው ዘርፍ አበረታች ሥራዎች ቢኖሩም የሚቀሩን በርካታ ሥራዎች በመኖራቸው በንድፈ ሃሳብ ዕውቀት የበለጸገና በክሂሎት የዳበረ የሰው ኃይል ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ የሥራ ላይ ልምምዶች በንድፈ ሃሣብ ያለን ዕውቀት በተግባር ለማዋሐድ የሚረዱ ሲሆን ለኢንዳስትሪውም መርሃ ግብሩን እንዲቃኝና እንዲያሻሽል ያደርጋል ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንደስትሪዎች ጋር መሥራታቸው የምርምር ሥራዎችና የዕውቀት ምንጮች ወደ ኢንደስትሪው ገብተው ለሀገር ልማትና የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት እንዲጠቅሙ የሚረዳ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶታል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በበኩላቸው በሥራ ላይ ልምምድ የቆዩ መምህራን ያመጡት ልምድና መልካም ተሞክሮ ሥርዓተ ትምህርቶችን ለማሻሻልና በምርምሩ መስክ ያልታዩ አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር መስፍን በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የተቀመጠው በተግባር ከሚሠራበት ሂደት ጋር ሰፊ ልዩነት እንዳለው በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል፡፡ ሪፖርቱ ወቅቱ የሚፈልገውን ምሩቃን ለማፍራት የትምህርት ሥርዓቱን ዳግም መቃኘት እንደሚገባ ያሳየና የንድፈ ሃሳብ አቀራረቦች ላይ የማሻሻያ ጥቆማዎች የተሰጡበት ነው፡፡ በተቋማትና በዩኒቨርሲቲው የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ከኢንደስትሪዎች፣ ከመንግሥትና ከግል ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ወሳኝ በመሆኑ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንና ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደሚሠሩም ዲኑ ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው በተገቢው ሁኔታ ተምረው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው የማብቃት ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ከኢንደስሪዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራትና ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መምህራኑ የቀሰሙት የተግባር ልምድ ለተማሪዎቻቸው ጠቃሚ ዕውቀት ለማስተላለፍ የሚያግዝ፣ የምርምር ልምድ የሚያካብትና የኢንደስትሪውን ችግር ለመፍታት የሚረዳ መሆኑን ዶ/ር ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የተቋማትና የኢንደስትሪ ኃላፊዎችና ተጠሪዎች በሰጡት አስተያየት የተቋማቸውን ክፍተቶች ያዩበትና ለቀጣይ ብቁ የሰው ኃይል ለማግኘት በጋራ እንዲሠሩ ዕድል የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በተግባር ላይ ልምድ ልውውጥ የቆዩ 5 መምህራን ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን መምህራኑ ከቆዩባቸውና ሌሎችንም ጨምሮ ከ9 ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የጳጉሜ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል አክስዮን ማኅበር፣ የኃይሌ ሪዞርት ሆስፒታሊቲ ግሩፕ፣ የኦዝ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ፣ የኮተቤ ብረታ ብረት ፋብሪካ፣ የኢትጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ ኢንደስትሪ ፓርኮችና ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ፣ የሀዋሳ ሮሪ ኢንተርናሽናል ሆቴል እና የወላይታ ዞን አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር መምሪያ ኃላፊዎችና ተጠሪዎች እንዲሁም የጋሞ ዞን የተለያዩ ሴክተሮች ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት