በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህራን የተገኘ የምርምር ውጤት ላይ ተመሥርቶ ኮሌጁ ከዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት፣ ከጃኖ ዕደ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ እና ከGIZ ጋር በመተባበር በጨንቻ ዶኮ ማሾ ቀበሌ ለሚኖሩ ሸማኔዎች የዘመናዊ ሽመና አሠራር ላይ ከግንቦት 20 - ሰኔ 04/2014 ዓ/ም ለ15 ተከታታይ ቀናት የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በቀበሌው በሽመና ሥራ በማኅበር የተደራጁ 127 ግለሰቦች እንዳሉ ጠቅሰው የሚሠሩት የሽመና ሥራ ዘመናዊነትን ያልተላበሰና ኋላ ቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሠራሩን ለማዘመን በድጋፍ የተገኙ 20 ማሽኖች ግብዓት ያልተሟላላቸው በመሆኑ አስፈላጊ ግብዓት ከህንድ ሀገር በማስመጣትና ተቀራራቢነት ያላቸው 13 ማሽኖችን ከሀገር ውስጥ ግዢ በመፈፀም በአጠቃቀማቸው ላይ ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ይህም በዋናነት የሸማኔዎቹን ድካም የሚቀንስና የገቢ ምንጫቸውን የሚያሳድግ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ቴክኖሎጂውንም ሆነ ሥልጠናውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዳረስ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በባህሪው ትስስር የሚፈልግ በመሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት፣ ምርቱን ከገበያ ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም ለምርት ማሳያና መሸጫ ስፍራ በማዘጋጀት ረገድ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ቴክኖሎጂውን በዩኒቨርሲቲው ሜካኒካል ምኅንድስና ት/ክፍል በኩል በተቋሙ መሥራት ቢቻል ለግዢ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑን ዲኑ ጠቁመዋል፡፡ 

የፕሮጀክት መነሻ ጥናቱን ካጠኑት አንዱ የሆኑት የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ አወል በክር ጥናታቸው በሽመና ሥራ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በግብዓት አቅርቦትና ገበያ ትስስር ዙሪያ ያሉባቸውን ችግሮች በመቅረፍ ምርታቸውን የሚያሳድጉበትንና የገበያ ሥርዓታቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገድ ለማመላከት የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ወደ ማኅበረሰቡ ለማውረድ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ለሥራው የሚያግዙ አክሰሰሪ የሌላቸውን 20 ማሽኖች በድጋፍና 13 በግዢ ልናገኝ ችለናል ብለዋል፡፡

አሠልጣኝ እስማኤል ጀማል ሥልጠናው ከባህላዊ አሠራሮች የተለዩ ዲዛይኖች በሚሠሩባቸው መንገዶች ላይ በማተኮር የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ሸማኔዎቹ ከነጠላና ጋቢ ባሻገር አዲሱን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የወንበር፣ የሶፋና የአልጋ ልብሶች፣ መጋረጃ፣ የጽዳት ፎጣዎችና የመሳሰሉትን መሥራት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

የጃኖ ዕደ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ መሥራችና ባለቤት አቶ ፍሬው ቆንጆ ከዚህ ቀደም ድርጅታቸው ከGIZ ዘመናዊ የሽመና ማሽን ድጋፍ ቢያገኝም ማሽኖቹ ግብዓት ያልተሟሉላቸው ነበሩ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ማሽኖቹ የጎደሏቸውን ግብዓቶች በማሟላት ለሸማኔዎቹ ለማስረከብ በማቀዱ ማሽኖቹን መለገሳቸውን አቶ ፍሬው ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ቴክኖሎጂው ፍጥነትን የሚጨምር፣ ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብ፣ የምርት መጠንን በመጨመር የኢኮኖሚ ሁኔታችንን የሚያሳድግልንና የአካላዊ ጫና ጉዳትን የሚቀርፍ ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት