አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ኤይድ/Christian Aid /ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በካምባ ወረዳ ዲንጋሞ ቀበሌ ማይጸሌ ወንዝ ላይ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ለማስገንባት ሰኔ 12/2014 ዓ/ም የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ ለሥራው ማስፈፀሚያ የሚሆነው ገንዘብ 1.1 ሚሊየን ብር በዩኒቨርሲቲውና 6.123 ሚሊየን ብር በክርስቲያን ኤይድ ግብረ ሠናይ ድርጅት የሚሸፈን ይሆናል፡፡

የአካባቢውን የመብራት ችግርና ተፈጥሯዊ መልካም አጋጣሚዎች ታሳቢ አድርጎ የፕሮጀክት ምርምሩ መጀመሩን የዩኒቨርሲቲው መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ በየነ ፈየ ገልጸዋል፡፡ በቂ የውሃ ፍሰት፣ የውሃ ከፍታ፣ በአካባቢው ያለ ሕዝብ፣ አካባቢው ከዋናው የኃይል አቅርቦት ያለው ርቀት እና ሌሎችም ቴክኒካዊ ነገሮች ተጠንተው ወደ ትግበራ መገባቱን የተናገሩት አስተባባሪው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ከ5-10 ኪሎ ዋት የኤክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭና 600 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከዋናው ማዕከል ኃይልን ከመጠበቅ ይልቅ ዩኒቨርሲቲው አጋሮችን በማሳተፍ አካባቢያዊ ሀብትን ተጠቅሞ ለመሥራት መነሳቱ አርአያ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ግቡን እንዲመታና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆኖ ለማየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የራሱን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት ሀገራችን ካሏት ተፋሰሶችና የውሃ ሀብት አንፃር በተለይም በገጠሩ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነቱ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን መሰል አነስተኛ የኃይል ማመንጫ አማራጮችን መጠቀም ችግሩን በየደረጃው ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው ጀምሮ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን መቆየቱን የጠቀሱት ፕሬዝደንቱ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ግንባታው የአካባቢውን የመብራት ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር ት/ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የክርስቲያን ኤይድ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ ይጥና ተካልኝ ድርጅታቸው የልማትና ሰብዓዊ ድጋፎች የሚያደርግና የኅብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል የሚሠራ እንደመሆኑ የካምባ ወረዳ ዲንጋሞ ቀበሌ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀደውን ፕሮጀክት በገንዘብ መደገፉን ገልጸዋል፡፡ መሰል አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል በሙከራ ደረጃ ተሠርቶ ውጤታማ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የዲንጋሞ ኃይል ማመንጫ ሥራ እውን እንዲሆን ከድርጅታቸው በተጨማሪ የአካባቢው አስተዳደርና ኅበረተሰቡ ከዩኒቨርሲቲው ጎን መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የካምባ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዳመነ ነጋሽ ወረዳቸው ለእርሻ፣ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለቱሪዝም፣ ለማዕድንና ኢነርጂ ዘርፎች ምቹ የሆነ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉት ቢሆንም ከመሠረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተያይዞ

የሚፈለገውን ያህል አቅሙን አልተጠቀመም ብለዋል፡፡ ከመሠረተ ልማቶቹ አንዱ የኤክትሪክ ኃይል መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው ዩኒቨርሲቲው አጋር ተቋማትን በማሳተፍ ከወረዳው ቀበሌዎች አንዱ የሆነውን የዲንጋሞ ማኅበረሰብ የመብራት ችግር ለመቅረፍ ሥራ መጀመሩ ባለ ውለታ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ለሥራው ስኬት ወረዳውና የወረዳው ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የሰው ኃይል ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮና የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ፍሬው ተስፋዬ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የደቡብ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አጸደ አይዛ፣ የክርስቲያን ኤይድ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ ይጥና ተካልኝ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዝደንቶች፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና የፕሮጀክቱ ተመራማሪዎች፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፣ የካምባ ወረዳ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ በመርሃ ግብሩ ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት