በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ትምህርት ክፍሎች የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ እጩ ዶክተሮች ከሰኔ 4-8/2014 ዓ.ም የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎች በተገኙበት የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ የምርምር ሥራቸውም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በመገኘቱ በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹Effects of ICT Assisted English Language Teaching Training on EFL Teachers’ Technological, Pedagogical, Content Knowledge, Attitude and Practice›› በሚል ርዕስ ሰኔ 4/2014 ዓ/ም ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት እጩ ዶ/ር ምሕረተአብ አብርሃም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል ላለፉት አምስት ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ እጩ ዶ/ር ምህረተአብ ትውልድና እድገታቸው በሀዲያ ዞን ጊምቢቹ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ አጠናቀዋል፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ያገኙ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርና የፕሮግራም አስተባባሪ እንዲሁም በFM 97.7 ‹‹አዲስ መንገድ›› እና በFM 100.9 ‹‹ከምርምር ዓለም›› የተሰኙ የሬድዮ ፕሮግራሞች መሥራችና ተባባሪ አዘጋጅ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡

ሌላኛው እጩ ዶ/ር ቶማስ ቶማ የመመረቂያ ጽሑፋቸው ‹‹Vulnerability Management Practices and Livelihood Security Status in Gamo Lowlands of Southwest Ethiopia›› በሚል ርዕስ የተከናወነ ሲሆን ሰኔ 6/2014 ዓ/ም ለግምገማ ቀርቧል፡፡ እጩ ዶ/ር ቶማስ በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቦረዳ 1ኛ ደረጃ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨንቻ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች አጠናቀዋል፡፡ ከሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በጂኦግራፊ ትምህርት ዲፕሎማ ያገኙ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ እና 2ኛ ዲግሪያቸውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ ትምህርት አግኝተዋል፡፡ እጩ ዶ/ር ቶማስ በመምህርነትና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ ቆይተው የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል አግኝተው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል፡፡

በሌላ በኩል እጩ ዶ/ር ታሪኩ ዘካሪያስ ‹‹Wetland Degradation: Driving Forces and Livelihood Benefits in the Western Shores of Lake Abaya-Chamo, Rift Valley of Ethiopia›› በሚል ርዕስ ሰኔ 6/2014 ዓ/ም ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ እጩ ዶ/ር ታሪኩ ውልደትና እድገታቸው በጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በካምባ 1ኛ ደረጃ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ እጩ ዶ/ር ቶማስ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጂኦግራፊ ትምህርት ያገኙ ሲሆን በሰመራ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በት/ክፍል ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡

‹‹Impacts of Soil and Water Conservation Measures on Erosion Risks, Soil Fertility, and Rural Livelihoods in the Damota Area Districts, Southern Ethiopia›› በሚል ርዕስ እጩ ዶ/ር ማሙሽ ማሻ ሰኔ 7/2014 ዓ/ም ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡

እጩ ዶ/ር ማሙሽ በወላይታ ዞን የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በገሱባና በሶዶ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በጂኦግራፊ ትምህርት አግኝተዋል፡፡ እጩ ዶ/ር ማሙሽ በመቱ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በዲፓርትመንት ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡

‹‹Socio-Ecological Drivers of Mammalian Diversity and Human-Carnivore Coexistence in Faragosa-Fura Landscape of Southern Rift Valley, Ethiopia›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ሰኔ 8/2014 ዓ/ም ያቀረቡት እጩ ዶ/ር ብርሃኑ ጌቦ በጋሞ ዞን ምዕራብ ዓባያ ወረዳ የተወለዱ ሲሆን ከሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በባዮሎጂ ትምህርት ዲፕሎማ፣ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ እና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 2ኛ ዲግሪያቸውን በማይክሮ ባዮሎጂ አግኝተዋል፡፡ እጩ ዶ/ር ብርሃኑ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ በመምህርነት፣ በአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመምህርነትና በምክትል ዲንነት፣ በወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት፣ በዞን ትምህርት ቢሮ እና በተለያዩ ቦታዎች በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡

የድኅረ ምረቃ ት/ቤት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ ዩኒቨርሲቲው በድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንና በተለይም የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ እንዲጨርሱ እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አበራ በተለያዩ ፕሮግራሞች ከ230 በላይ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ቢሆንም ከሌሎች ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲነፃፀር ገና ብዙ መሠራት አለበት፡፡ በመሆኑም በ2015 ዓ/ም 12 የ2ኛና 8 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመጀመር የውስጥና የውጪ ግምገማ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በግምገማ መርሃ-ግብሩ የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎችን ጨምሮ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሮች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የት/ክፍል ኃላፊዎች፣ የዘርፉ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ታድመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት