Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፐሎማሲ ማዕከል ‹‹የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አሠራር፣ የሚዲያ አተገባበርና ንቃት›› በሚል ርዕስ ከዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ለተወጣጡ ከ200 በላይ ተማሪዎች ሰኔ 10/2014 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በርካታ ሀገራት ፐብሊክ ዲፐሎማሲን የሀገራቸውን ገጽታ ለመገንባት እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በዓለም አቀፍ ጫና ውስጥ ያሉ ሀገራት ያላቸውን እውነታ ዓለም እንዲገነዘበው ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡ ሀገራችን በአንድነት ፀንታ ጠንካራ መንግሥት እንዲኖራት ተማሪዎቻችን ራሳቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ብቁ በማድረግ፣ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀምና የሀገራቸውን እውነታ ለዓለም በማስገንዘብ የሀገራቸው ዲፕሎማት መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ በበኩላቸው መደበኛው የዲፕሎማሲ ሥራ ብቻውን ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ እንደ ሀገር ዘርፉን ለመደገፍ በማለም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም የፐብሊክ ዲፐሎማሲ ማዕከላት መቋቋማቸውን አስታውሰዋል፡፡ ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በመስኩ ግንዛቤን ከመፍጠር አኳያ ሥልጠናዎችን መስጠቱንና በዘርፉ የምሁራንን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ሀገራዊ የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በዋናነት ተማሪዎች የፐብሊክ ዲፐሎማሲን ምንነትና አሠራር እንዲሁም የሚዲያውን አተገባበር ተገንዝበው በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መልዕክቶችን በሰላ ዕይታ መመርመር እንዲችሉና ራሳቸውን ከአላስፈላጊ የሚዲያ ተጽዕኖ ነፃ እንዲያደርጉ ግንዛቤን ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ሚዲያ ሊትረሲ/Media Literacy/ የሚዲያን አሠራር የመመርመር እና በዜናም ሆነ በመዝናኛ መልክ የሚተላለፉ መልክቶችን እንዲሁ ከመቀበል ባሻገር “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉ ጥያቄዎችን በሰላ ዕይታ የማየት ብቃት ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ በሠለጠኑ ሀገራት የሚዲያ ሊትረሲ ትምህርት ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ማዕከሉ በሀገራችን ወጣቶች ላይ ሚዲያው እየፈጠረ ያለውን ተጽዕኖና በዚህም ምክንያት እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በጉዳዩ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ባሻገር በጋሞ፣ ጎፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ለሚገኙ ወጣቶች መሰል ሥልጠናዎችን ለመስጠት አቅዶ እየሠራ መሆኑንም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

ከአሠልጣኞች መካከል በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶ/ር ይሄነው ውቡ ‹‹ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንደ መልካም ዕድልና ተግዳሮት ከኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አረዳድ አንፃር›› በሚል ርዕስ በሰጡት ሥልጠና በዓለማችን በሚገኙ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በብዙ መልኩ ከቀድሞው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተቀየረ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡

እንደ አሠልጣኙ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተዋናዮች ቁጥር መጨመር፣ ሕዝቡ ለውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት መስጠቱና በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መድረኮች በዲፕሎማቶች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር መጀመሩ ለተፈጠረው የአሠራር ለውጥ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሁሉም መስኮች እርስ በእርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ይሄነው የሀገራችን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዚህ ውስብሰብ ግንኙነት ምክንያት የሚፈጠሩ እድሎችን አስፍቶ መጠቀምና የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን መቀነስ ላይ ማተኮር ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡

አሁናዊ የኢትዮጵያ ችግሮች በተናጠል ሳይሆን የውጭ ግንኙነትና ውስጣዊ ጉዳዮችን በጋራ እንድናይ የሚያስገድዱ ናቸው ያሉት አሠልጣኙ ውስጣዊ ችግሮችን መፍታትና አንድነትን ማጠናከር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት ላይ የሚደርሱ ውጫዊ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም አቅምን የሚያጠናክር በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ሀገራዊ ህልውናና የግዛት አንድነትን አደጋ ላይ የጣሉ ክስተቶች እንደነበሩና አሁንም መሰል አዝማሚያዎች እንደሚስተዋሉ የተናገሩት አሠልጣኙ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ዲፕሎማት በመሆን የዜግነት ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የኤሌክትሪካል ምኅንድስና እና የሃይድሮሊክስና ውሃ ሀብት አቅርቦት ምኅንድስና ተማሪዎች የሆኑት በረከት የደሜና ዘውገ አልታዬ መሰል ሥልጠናዎች ከትምህርታቸው ባሻገር በሌሎች ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ዕውቀት እንድንገበይ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የሀገራቸውን እውነታ ለማሳወቅ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት