Print

‹‹በተፈጠረው እድል ማኅበረሰባችንን እናገልግል›› በሚል መሪ ቃል ዩኒቨርሲቲው 7ኛውን የማኅበረሰብ ሳምንት ከሰኔ 06-12/2014 ዓ/ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአከባበር መርሃ ግብሩ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለበጎ አድራጎት በተሰበሰበ ከ400 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች ለ5 አባወራዎች የተረከቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ከአጋር ድርጅቶች ባገኘው ድጋፍ የገዛቸውና 4 ሚሊየን ብር ያህል ግምት ያላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ/ኮምፖስት ማቀነባበሪያ ማሽንና አነስተኛ የጭነት መኪኖች ለ6 ማኅበራት ተላልፈዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ባከናወናቸው ተግባራትና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያም ከአካባቢው ማኅበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ምርምሮችን ወደ ፕሮጀክት በመቀየር ተግባር ላይ እያዋለና ቴክኖሎጂ ማላመድና ማሻገር ላይ አፅንኦት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአፈፃፀም ጠንካራና ደካማ ጎኖቹ እንዲሁም ቀጣይ ትኩረት ማድረግ ያለበት ጉዳይ ላይ ከማኅበረሰቡና ባለ ድርሻ አካላት ግብዓት በመውሰድ የተሻሉ ሥራዎች ለመሥራት እንዲያግዘው የባለ ድርሻ አካላት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ መካከል አንዱ ‹‹የማኅበረሰብ አገልግሎት›› መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ስያሜው ባሳደረው የተዛነፈ የአመለካከት ተፅዕኖ ምክንያት ዩኒቨርሲቲውን ሁሌም ሰጪና የሌላውን ድጋፍ የማይፈልግ አድርጎ ማሰብን እንዳስከተለ ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ ‹‹የማኅበረሰብ ጉድኝት›› የሚለው እሳቤ የዩኒቨርሲቲውንና የማኅበረሰቡን በጋራ ማቀድ፣ ሀብት ማፈላለግ፣ ማከናወንና፣ ውጤትን መጠቀምን ያየዘ እና የተሻለ የእርስ በእርስ ቁርኝትን የሚያሳይ በመሆኑ ዘርፉን በተሻለ ይገልጸዋል ብለዋል፡፡ እሳቤው በተቋሙ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችንም የሚይዝ ሲሆን በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር፣ የልኅቀትና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች እንደ ማሳያ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ያከናወናቸው ዐቢይ ሥራዎችን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በመነሻ ጽሑፉ ዩኒቨርሲቲው በተቀናጀ የጎልማሶች ትምህርት፣ በፀሐይ ታዳሽ ኃይል፣ በባዮ ጋዝ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በትምህርት ቤቶች ድጋፍ፣ በጤና ተቋማትና የሕክምና አገልግሎት ድጋፍ፣ በንጹሕ የመጠጥ ውሃ፣ በሥልጠናና ሙያዊ ድጋፍ፣ በነፃ የሕግ አገልግሎት እና ሌሎችም ዘርፎች ያከናወናቸው ተግባራት የተመለከቱ ሲሆን በተጨማሪም የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ማኅበራት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

ዶ/ር ተክሉ ዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ቢሆንም ማኅበረሰቡ በሚጠብቀው ልክ የሰፉ ሥራዎችን ለመሥራት ዩኒቨርሲቲውን አገልግሎት አቅራቢ ብቻ አድርጎ ከሚያየው ተለምዷዊ አመለካከት መሻገርና ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ በቅንጅት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በዕለቱ ከተመረጡ 3 ፕሮጀክቶች፡- የእንሰት አመራረት ሂደትን ለማሻሻል የሚሠራው ኢኖቬቲቭ እንሰት ፕሮጀክት፣ የተሻሉ የግብርና ግብዓትና ዘዴዎችን ለአርሶ አደሩ የሚያስተዋውቀው ቤኔፊት ሪያላይዝ እና ዓባያና ጫሞ ሐይቆችና ተፋሰሶቹን ለመታደግ የሚሠራው AMU-IUC ፕሮጀክቶች የእስከ አሁን እንቅስቃሴን አስመልክቶ በፕሮጀክቶቹ ተመራማሪና አስተባባሪዎች ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡

በውይይት መነሻ ጽሑፉና በሪፖርቶቹ ላይ ተመሥርቶ ተሳታፊዎች መልካም አፈፃፀምና ድክመቶች ባሏቸው ነጥቦች ላይ ሰፊ አስተያየትና ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን መሻሻል በሚገባቸውና የወደ ፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት