የ‹‹International Youth Fellowship (IYF)›› ሊቀ መንበርና አስተሳሰብ ቀረጻ አስተምህሮ/Mindset Education/ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ቾው ሱንግዋ/Dr Cho Sunghwa/ ‹‹Public Lecture on Mindset›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የሕዝብ ገለጻ/Public lecture/ ሐምሌ 29/2014 ዓ/ም አቅርበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የአስተሳሰብ ቀረጻ ትምህርትን በስፋት መውሰድ ከግለሰብ አልፎ በሀገር ደረጃ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ም/ፕሬዝንቱ ገለጻ የዶ/ር ቾው ሱንግዋ ቡድን ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ሥልጠናውን እየሰጠ ሲሆን ሀገራቸው ደቡብ ኮሪያ በሕዝቦቿ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ በመሥራቷ ያመጣችውን ውጤትና የደረሰችበትን ደረጃ በማሳየት ተሞክሮ ያጋሩበት መድረክ ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዶ/ር ቾው ሱንግዋ ንግግራቸው በሰዎች የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በቅኝ ግዛትና ጦርነት ላይ የነበረች ደቡብ ኮሪያ በኢኮኖሚ የበለጸገችው በዋናነት የሕዝቡን አመለካከት መቀየር በመቻሉ እንደሆነና በኢትዮጵያም የሕዝቡ አስተሳሰብ ላይ መሥራት ከተቻለ የተሻለ ለውጥና እድገት ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ቾው የእያንዳንዱን ዜጋ የአስተሳሰብ ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ የወጣቶችንና አመራሮችን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ትኩረታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ አነስተኛ የሕዝብ መጠንና ደካማ ኢኮኖሚ እንዲሁም በሕዝቧ መካከል ክፍፍል የነበረ መሆኑ በቅኝ ገዢዋ ጃፓን ስር በቀላሉ እንድትወድቅ ቢያደርጋትም በሕዝቦቿ ብርቱ ትግል ነጻ መውጣት መቻሏን ዶ/ር ቾው ተናግረዋል:: ከቅኝ ግዛት ነጻነቷን ካገኘች በኋላ በዜጎቿ አስተሳሰብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ግንዛቤያቸው እንዲዳብር በመሠራቱ በፍጥነት ከድህነት ተላቃ ግዙፍ ኢኮኖሚ እንድትፈጥር አግዟታል ብለዋል፡፡

በተፈጥሮ ሀብት የታደለችውና ደቡብ ኮሪያን 10 እጥፍ የምትበልጠው ኢትዮጵያ ሕዝቧ በሰላምና በአንድነት ተግባብቶ ከሠራ የበለጠ ውብና የበለጸገች ሀገር መሆን ትችላለች ያሉት ዶ/ር ቾው ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ባለበት የትምህርት፣ የሥራ፣ የኃላፊነትና የመሪነት ደረጃ የጠባቂነት አስተሳሰብን ማራቅ፣ ለውጥን ከራሱ መጀመር፣ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ነገሮችን በተለያየ ዕይታ መመልከት፣ የእኔ ድምፅ ብቻ ይሰማ ከሚለው አስተሳሰብ በመውጣት የሌላውን በማዳመጥና ከሌላው በመማር ለችግሮች የመፍትሔ ሃሳብ መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር ቾው ለሀገራቸው ነጻነት ዋጋ ለከፈሉት የኢትዮጵያ ጀግኖችና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን የነጻነት ዋጋ እጅግ ውድ መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያ ከድህነት ነጻ እንድትወጣ ጠንክረው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ደቡብ ኮሪያ በቅኝ ግዛት ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ነጻ እስከወጣችበት ጊዜ ያሳለፈችውን ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም ችግሮችን ተቋቁማ አሁን እስከደረሰችበት ያለውን የእድገት ደረጃ በምስል የተደገፈ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ዶ/ር ቾው ሱንግዋና ቡድናቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በብሔራዊ ደኅንነት መ/ቤት፣ በጅግጅጋ፣ በባህር ዳርና ሰመራ መሰል መድረክ ማዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት