Print

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከደቡብ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲና ከደቡብ ክልል ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት ጋር በመተባበር በመሎ ኮዛ ወረዳ ጨልቆ ወንዝና በቡርጂ ወረዳ ሰገን ወንዝ ላይ ለሚያሠራቸው የግድብና መስኖ ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ነሐሴ 2/2014 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች አቅርቧል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ፕሮጀክቶቹ እስከ አሁን በተሠሩበት አቅምና ተነሳሽነት ከቀጠሉ ውጤታቸው ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡ ሥራውን ከሌሎች የመማር ማስተማርና አስተዳደራዊ ሥራዎች ጋር አመጣጥኖ መሄዱ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ኢንስቲትዩቱ ለማኅበረሰቡና ለሀገር የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን ስለመሥራቱ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ማሳያ የሚሆን ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መሰል የትብብር ሥራዎችም አስፈላጊነታቸው ጉልህ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በውሃ ዘርፍ መሰል ፕሮጀክቶችን መሥራቱ ገጽታውን ለመገንባት የሚጠቅመውና ሌሎች የትብብር ሥራዎችን የሚያስገኝ መሆኑን ተናግረው ሀገራችን ግብርናን ለማዘመን እየሠራች ላለችው ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ባለ ድርሻ አካላት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርና የፕሮጀክቶቹ ዋና ማኔጀር ዶ/ር አብደላ ከማል ከ7-9 ወራት የሚፈጁት ፕሮጀክቶች ከተጀመሩ 3ኛ ወራቸውን መያዛቸውን ጠቅሰው የፕሮጀክቶቹን ሂደት ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም መሰል ፕሮጀክቶችን በደቡብ ኦሞ ዞን በጥሩ ሁኔታ ሠርቶ ማስረከቡን ያስታወሱት ዶ/ር አብደላ አዲሶቹ ፕሮጀክቶች ቀጥታ በመንግሥት በጀት የሚሠሩ በመሆኑ ከቀደሙት ይለያሉ ብለዋል፡፡

የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር፣ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ታምሩ ተሰማ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው ፕሮጀክቶቹ በ2015 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ከታቀዱ በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል የሚገኙ ሲሆኑ በሰገን ወንዝ ላይ የሚከናወነው ፕሮጀክት የቡርጂ አካባቢና ኮንሶ ዞንን በከፊል እንዲሁም በጨለንቆ ወንዝ ላይ የሚካሄደው ፕሮጀክት የመሎ ኮዛ አካባቢን ያለማሉ፡፡

ፕሮጀክቶቹ በተደጋጋሚ ለረሃብና ለድርቅ የሚጋለጡ አካባቢዎችን በመስኖ በማልማት ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው መምህራን በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያስተምሩ፣ ዩኒቨርሲቲው የመሥራት አቅሙን እንዲያሳይና በሌሎችም ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ እድል የሚፈጥር መሆኑን ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅ በተለያዩ የአፈጻጸም ምዕራፎች ከሁለቱ ኢንስቲትዩቶች፣ ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ከማኅበራዊ ሳይንስና ስነሰብ እና ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች የተወጣጡ 28 መምህራን የሚሳተፉ መሆኑን የፕሮጅክቱ አስተባባሪ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ታምሩ በፕሮጀክቶቹ የእስከ አሁን ሂደት የመስኖውን ዋና አውታር የመለየት፣ መረጃ የማሰባሰብና የኢንሴፕሽን ሥራ፣ የፕሮጀክቱን ሠነድ ዝግጅት በማጠናቀቅ ማስገምገምና ማስጸደቅ፣ የፕሮጀክቱ መገኛ ቦታ በዓለም አቀፍ ካርታ ውስጥ እንዲካተት መደረጉ፣ የሳይት ቅየሳ በማድረግ 18 የመቆጣጠሪያ ችካሎች /Control Points/ መተከልና በተለይ የጨልቆ ወንዝ መስኖ ፕሮጀክት ግድብ ማረፊያ ቦታና በአቅራቢያው ሊለማ የሚችል 1 ሺህ ሄክታር መሬት የመለየት ሥራዎች ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

በፕሮግራሙ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛን ጨምሮ ም/ፕሬዝደንቶች፣ የቴክኖሎጂና የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ማኅበር ተወካይና የፋከልቲው መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት