ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከ አሁን ባለው አፈጻጸም የሦስቱም ዙሮች የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቆ 2ው ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ለመግለጽ ይወዳል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የምትኖሩ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ባለ ድልና ባለ ዕድል ትውልድ ለመሆን አበቃን፡፡ 

ሀገራችን ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶቿን በአግባቡ በመጠቀም ያሉባት የንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የመስኖ ግብርና ችግሮች እንዲፈቱ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ከተቋቋመበት ከ1979 ዓ/ም ጀምሮ በተለይ በውሃ ምኅንድስና ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሠልጠን በተለያዩ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮክቶች ላይ በሙያቸው በማገልገል የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ምሁራንና ባለሙያዎችን ሲያፈራ ቆይቷል፡፡

በውሃ ምርምርና በሌሎችም የልኅቀት ማዕከላት በትኩረት እየሠራ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው በውሃ ዘርፍ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችን ተቀባይነትና ተደራሽነት ባላቸው ዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ በማሳተም፣ የውሃ ምርምር ማዕከልና ቤተ-ሙከራዎችን አቅም በማሳደግና ዓለም አቀፍ መስፈርት እንዲያሟሉ በማድረግ እንዲሁም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር አዲስ በተቋቋመው ‹‹የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም›› በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የውሃ ሀብት አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ሀገራችን ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቶቿ ተጠቃሚ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ለማገዝ እየሠራ ይገኛል፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በውሃ ሀብቶችናበውሃ ሀብቶችና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንዲሁም በውሃ መሠረተ ልማቶች ወይም ፕሮጀክቶች ዙሪያ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በመተባበር ለሚመለከተው አካል ሳይንሳዊ መረጃ በመስጠት መደገፉን በትኩረት የሚቀጥልበት ይሆናል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ታላላቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተሠሩ ያሉበትና እንደ ሀገር የረዥም ጊዜ ምኞትና ቁጭት ፍሬ ማየት የተጀመረበት ወቅት ላይ በመድረሳችን ብሎም የህዳሴው ግድብ 3 ዙር ሙሌት በስኬት ተጠናቆ 2ው ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ዩኒቨርሲቲው የተሰማውን ልባዊ ደስታ እየገለጸ መላው ኢትዮጵያውያንና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለይም የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምሁራን፣ ተማሪዎችና የቀድሞ ምሩቃን እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ይላል፡፡

ነሐሴ 6/2014 ዓ/ም

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት