“ኢትዮጵያን እናልብሳት!” እና “Green Legacy; Green Campus!” በሚሉ መሪ ቃሎች በ4ው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በቤሬ ተፋሰስና በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ከነሐሴ 12/2014 ዓ/ም ጀምሮ 25,000 ችግኞችን እንደሚተክል ተገልጿል፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማልማትና የተፈጥሮ ደኖች ባሉበት እንዲቆዩ የመጠበቅ መጠነ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 25,000 ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡

በቤሬ ተራራ ላይ ለተፋሰሱ የሚሆኑ እንደ ወይበታ፣ ወይራ፣ ኮሪና የመሳሰሉ ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን በየካምፓሶቹ ለምግብነት የሚውሉ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ግሽጣ፣ ፓፓዬና ቡና እንዲሁም የተለያዩ የውበት ዛፎች እንደሚተከሉ ዶ/ር ተክሉ ገልጸዋል፡፡

የ4ው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በነገው ዕለት ነሐሴ 12/2014 ዓ/ም ከጠዋቱ 2፡30 በቤሬ ተራራ ተፋሰስ በሚከናውን የችግኝ ተከላ በይፋ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት