ዓለም አቀፍ የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት (GIS) ሶፍትዌር፣ የዌብ ጂ.አይ.ኤስና የጂኦዳታቤዝ አስተዳደር መተግበሪያዎች አቅራቢ ድርጅት የሆነው ‹‹Environmental Systems Research Institute (ESRI)›› በአሜሪካን ሀገር ሳንዲያጎ-ካሊፎርኒያ ከሐምሌ 01-09/2014 ዓ/ም ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ‹‹ESRI User Conference›› እና ‹‹Education Summit›› ላይ የተገኘው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር ኢትዮጵያን ወክሎ ለዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ግብ ስኬት የሚረዱ መረጃዎችን እንዲያሰባስብ ከስምምነት መደረሱ ተገልጿል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትን ለማስመዝገብ የሚረዷት ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንድትችል ዘርፉን በማሳደግ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመሪነት ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህንን ኃላፊነት ከመቀበል አንጻር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትብብሮችን ፈጥሮ ሥራዎች መጀመሩን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው በማቋቋም ላይ ላለው የጂአይኤስ ቤተ ሙከራ የሚረዱ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና ከዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት በኮንፍረንሱ መሳተፉ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቆይታችን በሁሉም የትምህርት መስኮች፣ በሦስቱ  የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ሥራዎች ጂአይኤስን የመጠቀም ልምድ የቀሰምንበት እንዲሁም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት ግንኙነቶችን የፈጠርንበት ነው ብለዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ የጉዞው ዓላማ ከESRIና አብረውት ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ዘላቂ ግንኙነት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ጠቅሰው በቆይታቸውም ከESRI ፕሬዝደንት Jack Dandermond፣ በመላው ዓለም የESRI ሶፍትዌሮችን የሚጠቀሙ ከ11 ሺህ በላይ ዩኒቨርሲቲዎችን በበላይነት ከሚያስተዳድረው ‹‹ESRI Global Education Manager›› እና ከሌሎችም የዩኒቨርሲቲና የተቋማት መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ስምምነቶችን ተፈራርሞ በተማሪዎች የትምህርት እድል፣ በጋራና በድጋፍ ፕሮጀክቶችና በሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ በጋራ ለመሥራት ከ‹‹Redlands University››፣ ‹‹University of Minnesota›› እና ‹‹University of Michigan›› ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጂአይኤስና ሪሞት ሴንሲንግ መምህርና AMU-ESRI ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ደንበል ቦንታ ከዚህ ቀደም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ሕጋዊ ፈቃድ/License/ የሌላቸው ሶፍትዌሮችን ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው ከኮንፍረንሱ ቀደም ብሎ ከESRI ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማር፣ ለምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራና ለአስተዳደራዊ ሥራዎች የሚውል ‹‹ArcGIS›› ሶፍትዌርን ለ3 ዓመታት በነፃ የመጠቀም ፈቃድ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ሶፍትዌሩ በሥሩ በርካታ መተግበሪያዎችን የያዘና መረጃዎችን ለመሰብሰብና ለመተንተን የሚወስደውን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት የሚያስቀር በመሆኑ ሕጋዊውን ሶፍትዌር የመጠቀም እድል ማግኘት የመረጃ ተአማኒነትንና የምርምር ሥራዎችን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት የሚጨምር ነው፡፡ ይህን ፈቃድ ከሰጠው ESRI ጋር የተጀመሩ ግንኙነቶች ለማጠናከር፣ የተለያዩ አዳዲስ ግንኙነቶችን ለመፍጠርና ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ሊሠራ ላሰባቸው ሥራዎች መሠረት ለመጣል በኮንፍረንሱ መገኘታችን ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ESRI በሚያካሂዳቸው የተጠቃሚዎች ኮንፍረንስ ላይ በዩኒቨርሲቲ አመራር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መገኘቱን የጠቀሱት አስተባባሪው ይህም ዩኒቨርሲቲው ለዘርፉ የሰጠውን አጽንኦትና በጋራ የመሥራት ተነሳሽነት ያሳየ እንዲሁም ቀጣይ ሥራዎችን በበለጠ መግባባትና ቅልጥፍና ለመሥራት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም ከቤልጂየም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ከዚህ ቀደም አመርቂ የትብብር ሥራዎችን መሥራቱን የገለጹት የAMU-IUC ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደ ዩኒቨርሲቲ አድማሱን ማስፋትና የሌሎችንም ሀገራት ተሞክሮ ማየት አስፈላጊ በመሆኑ በኮንፍረንሱ ላይ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዘላቂ ልማትንና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በተመለከተ ዓለም አቀፍ አሳሳቢነት ያለውና ሁሉም ተቀናጅቶ ሊሠራበት እንደሚገባ ግንዛቤ ላይ የተደረሰ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ፋሲል በዚህ ረገድ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጂአይኤስን የመሳሰሉ በቦታና በጊዜ የተወሰኑ መረጃዎችን አቅርቦ በመውሰድ ዓለምን ወደ አንድ መንደር ለማምጣት የሚችሉ ትላልቅ የቴክኖሎጂ እመርታዎች አላቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ፋሲል AMU-IUC 2 ምዕራፉን ሲቀጥል ከዚህ ቀደም የተገኙ ዕውቀቶችን ለማኅበረሰቡ ማውረድን የሚጠይቅ በመሆኑ በዋናነት ለአካባቢው ማኅበረሰብ የጠቀመውን እና ለሀገርና ለዓለም ዘላቂ ልማት ዕቅድ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ መሠረት አድርጎ መለኪያዎች ተቀምጠዋል፡፡ መለኪያዎቹ ውስብስብና የጂአይኤስ መረጃ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ከAMU-ESRI ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በትብብር መሥራት በሚቻልበት መንገድና ሁሉም የIUC ፕሮጀክቶች ጂአይኤስን በምን አቅም መጠቀም እንዳለባቸው የኮንፍረንሱ ቆይታቸው መረዳትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ከ142 ሀገራት የተወጣጡ 14,966 ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ፣ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ፣ የAMU-IUC ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እና የጂአይኤስና ሪሞት ሴንሲንግ መምህርና AMU-ESRI ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ደንበል ቦንታ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት