በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ባዮሎጂ ት/ክፍል በ‹‹Infectious Disease›› የ3ኛ እንዲሁም በ‹‹Medical Entomology and Vector Control›› የ2ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በ‹‹NORHED-SENUPH II›› ፕሮጀክት ድጋፍ ለሚከታተሉ ተማሪዎች በሞሎኪዩላር ባዮሎጂ ቤተ-ሙከራ የሚገኙ የተለያዩ የ‹‹Polymerase Chain Reaction (PCR)›› ማሽኖችን ለምርምር ሥራዎች በመጠቀም ዙሪያ ለ3 ሳምንታት የቆየ ሥልጠና ከሐምሌ 25/2014 ዓ/ም ጀምሮ ተሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የNORHED-SENUPH II ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ፈቃዱ ማሴቦ ሥልጠናው በዋናነት የምርምር ሥራቸው በፕሮጀክቱ ለሚደገፍ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ሥልጠናው ‹‹Conventional›› እና ‹‹Real Time›› PCR ማሽኖችን በተለያዩ መንገዶች መጠቀም ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡ በመስኩ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችን ተጨማሪ አቅም በመፍጠር ማሳላጥና ተማሪዎች ማሽኖቹን ለምርምር ሥራቸው በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስቻል የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ፈቃዱ ሥልጠናው በዋናነት በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመጡ ምሁር መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ እንደ ኮሌጅ ያለውን አቅም ለማጎልበት በማለም መምህራንም በሥልጠናው መሳተፋቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጡት አሠልጣኝ ሆሊ ጆይስ/Holly Joyce/ እንደገለጹት በሕክምናና ባዮሜዲካል ምርምር ቤተ-ሙከራዎች ውስጥ PCR በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ የዘረመል/DNA/ ትንንሽ ክፍሎችን ለማጉላት፣ የዘረመል ቅጂዎችን ለመሥራት፣ በኢንፌክሽን ወቅት በሽታ አምጪ ተህዋሲያን መኖር አለመኖራቸውን ለመለየትና ለሌሎች በርካታ ተግባራት የሚውል መሳሪያ ነው፡፡ በኮሌጁ የሚገኘው የሞሎኪዩላር ባዮሎጂ ቤተ-ሙከራ አደረጃጀት ለዚህ ሥራ አጋዥ በሆኑ መሳሪያዎችና ግብአቶች የተሟላ መሆኑን የጠቆሙት አሠልጣኟ ይህም በመስኩ ችግር ፈቺ አዳዲስ ዕውቀቶች የሚፈልቁባቸው ውጤታማ ምርምሮች እንዲከናወኑ ያግዛል ብለዋል፡፡ በሕክምናና ባዮሜዲካል መስኮች ለሚደረጉ የምርምር ሥራዎች PCRን መጠቀም የግድ መሆኑን የጠቀሱት አሠልጣኟ በዩኒቨርሲቲው በመስኩ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች መሳሪያውን ወደ ፊት ለሚያከናወኑት የምርምር ሥራ በአግባቡ መጠቀም የሚያስላቸው የተለያዩ የአሠራር ዘዴዎችን በተግባር የሚመለከቱበት ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የ‹‹Infectious Disease›› የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ መሐመድ ሰኢድ ከዚህ ቀደም በሁለቱም የPCR ማሽኖች አጠቃቀም ዙሪያ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ግንዛቤ እንደነበረው ተናግሮ በዚህ ሥልጠና በተግባር የተደገፈ ግንዛቤና ክሂሎት ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ በቀጣይ የሚሠራው የምርምር ፕሮጀክት ወባ ላይ ያተኮረ መሆኑን የተናገረው ሠልጣኙ ከሥልጠናው በተግባር ያገኛቸው የመሳሪያው አጠቃቀም ዘዴዎች ለምርምር ሥራው በእጅጉ የሚያግዙት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የ‹‹Medical Entomology and Vector Control›› የ2ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነችው ርብቃ ጌቱ በበኩሏ እየተከታተለች በምትገኘው የትምህርት መስክ የምርምር ሥራ ለማከናወን PCR ማሽንን መጠቀም የግድ መሆኑን ተናግራ ሥልጠናው ከዚህ አንፃር በእጅጉ የሚጠቅም ነው ብላለች፡፡ ከሥልጠናው በመሳሪያው አጠቃቀም ዘዴዎች ዙሪያ በተግባር የተደገፈ ግንዛቤ ያገኘች መሆኗንም ተናግራለች፡፡


የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት