በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃና አስተዳደር የ2ኛ ዲግሪ (MSc in Biodiversity Conservation and Management) እና በአካባቢያዊ ሳይንስ የ3ኛ ዲግሪ (PhD in Environmental Science)የትምህርት መርሃ ግብሮች ነሐሴ 9/2014 ዓ/ም የሥርዓተ ትምህርት የውጭ ግምገማ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ መርሃ ግብሮቹ የሴኔት የትምህርት ፈቃድ፣ የውስጥ ግምገማ፣ የውጭ ዳሰሳ ጥናትና ሌሎችንም ሂደቶች አልፈው እዚህ መድረሳቸውን ተናግረው በሥርዓተ ትምህርት ግምገማው የ‹‹Independent Study Course›› አፈጻጸም፣ የምርምሮች፣ የመማሪያ ግብአቶች እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር የተገናኙ ሃሳቦች ተነስተው ጥሩ ግብዓቶች እንደተገኙ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች የትምህርት ክፍሎችም በዚሁ አግባብ የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮችን እያዘጋጁ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

የስነ ሕይወት ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት ክምችት የታደለና የማኅበረሰብ ስብጥር ያለበት በመሆኑ በብዝሃ ሕይወት ዘርፍ የመሥራት እድሎች ሰፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የት/ክፍሉ መምህር ዶ/ር ዓለማየሁ ኃይለሚካኤል ዩኒቨርሲቲው በአካባቢያዊ ሳይንስ የ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ለ10 ዓመታት ያህል ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው ወደ 3ኛ ዲግሪ ለማሳደግ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢያዊ ሳይንስ ት/ክፍል መምህርና አስተባባሪ ዶ/ር ሽቴ ጋተው አካባቢ ሳይንስ ሰፊና በርካታ የትምህርት ዘርፎችን የያዘ በመሆኑ በድኅረ ምረቃ መርሃ ግብር በዩኒቨርሲቲው መከፈቱ ለዘርፉ መምህራንና መማር ለሚፈልጉ ሁሉ ትልቅ እድል ነው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት