የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ለሳውላ፣ ጨንቻ፣ ጫኖ ዶርጋ፣ ጻይቴና ጋርዳ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ ወጣት ማዕከላት በተለያዩ የትምህርት አይነቶች የተዘጋጁ የማጣቀሻና ልብ ወለድ መጻሕፍትን ሐምሌ 10/2014 ዓ/ም አበርክቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ማኅበረሰብ ተኮር ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው የመጻሕፍት ድጋፉ በተለያየ ጊዜ በቀረቡ ጥያቄዎች መሠረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ት/ቤት 25 አይነት በብዛት 200 መጻሕፍት የተበረከቱ ሲሆን በጠቅላላ 400,000 ብር ወጪ ተደርጎ ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ በአብዛኛው የገጠር ወረዳዎች የማጣቀሻ መጻሕፍት አቅርቦት አናሳ በመሆኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል አዳጋች አድርጎታል ያሉት ዳይሬክተሩ ድጋፉ ይህን ችግር በመቅረፍ ተማሪውን ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

አክለውም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት እንደ ዞንም ሆነ እንደ ሀገር ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች በቀጣይ ለሚጠብቃቸው ሀገራዊ ፈተና ዝግጅት ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በቤተ መጻሕፍት ተቀምጦ ለቀጣይ ትውልድ ለማጣቀሻነት እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መምህርት ፍቅርተ ሥዩም መጻሕፍቱ ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ማጣቀሻ መሆናቸውን ገልጸው ድጋፎቹ ቀጣይ እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ በዚህም ቀርበው መጠየቅ ላልቻሉ፣ ርቀው ላሉና እድሉን ላላገኙ ት/ቤቶችም ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘርይሁን መሰለ በበኩላቸው ድጋፉ በየትምህርት ቤቱ ያሉ በርካታ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረው በቀጣይ በሚኖረን ሥራ በመናበብና ፍላጎቶችን በዕቅድ በማመላከት ዞኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀናጅቶ ቢሠራ በዕውቀት የዳበረ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ማፍራት ያስችለናል ብለዋል፡፡

በድጋፍ መርሃ ግብሩ የተገኙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የታችኛው የትምህርት ደረጃ ላይ ላለው ትውልድ በማሰብ ድጋፍ ማድረጉ በት/ቤቶች ላይ የሚታዩ በርካታ ችግሮችን የሚቀርፍ፣ ደረጃውን ለማሻሻል የሚረዳና ለትምህርት ጥራት መሻሻል የሚያግዝ በመሆኑ በድጋፉ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የወጣቶች ማዕከላትን ለንባብ ምቹ በማድረግ ከተለያዩ ሱሶች ተጋላጭነት መታደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ አጭር የሥራ አቅጣጫ ውይይት ተደርጎ ከተሳታፊዎች ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥዋል፡፡


የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት