አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹አሻራችን ለትውልዳችን›› እና ‹‹Green Legacy; Green Campus!›› በሚሉ መሪ ቃሎች በቤሬ ተፋሰስ ችግኝ በመትከል ነሐሴ 12/2014 ዓ/ም 4ኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምሯል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በቀደሙት መርሃ ግብሮች ከተተከሉት ችግኞች መካከል 90 በመቶው መጽደቃቸውን ገልጸው በዘንድሮው መርሃ ግብር የሚተከሉት ችግኞች በአካባቢው በቀላሉ እንደሚበቅሉ በጥናት የተረጋገጡና ከአካባቢው የአየር ሁኔታ አኳያ ድርቅን ሊቋቋሙ የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የመንከባከብና የመከታተል ሥራ ወሳኝ ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ የተተከሉት ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲጸድቁ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እንደሚሠራና ይህንንም በዋናነት የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት በባለቤትነት የሚመራው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ከአካባቢው ምኅዳር ጋር የሚስማሙና ድርቅን የሚቋቋሙ ችግኞች መተከላቸው የመጽደቅ መጠኑን ከፍ እንደሚያደርገውና ምንጮችና የውሃ አካላት የመድረቅ አደጋ አንዳይገጥማቸው የሚከላከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአካባቢ ጥበቃና ከውበት ዛፎች በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎች መካተታቸው የሚያስደስት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ላለፉት በርካታ ዓመታት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማልማትና የተፈጥሮ ደኖች ባሉበት እንዲቆዩ የመጠበቅ መጠነ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች 8 የችግኝ ጣቢያዎች እንዳሉት የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ ዩኒቨርሲቲ 25,000 ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ለቤሬ ተራራ ተፋሰስ የሚሆኑ የወይበታ፣ ወይራና ኮሪ በአጠቃላይ 13,000 ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በቀጣይም በየካምፓሶቹ ለምግብነት የሚውሉ የማንጎ፣ አቮካዶ፣ ግሽጣ፣ ፓፓዬና ቡና እና የተለያዩ የውበት ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል፡፡ በዕለቱ የነበረው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተሳትፎ አበረታች መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዕለቱ በመገኘት አሻራቸውን ማስቀመጣቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው የተተከሉ ችግኖች እንዲጸድቁ ክትትል ማድረግና መንከባከብ ይኖርብናልም ብለዋል፡፡

በችግኝ ተከላው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት