የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ/ICT/ ዳይሬክቶሬት ከኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር እና ከኤሌክትሪካልና ኮሚፒውተር ምኅንድስና ፋከልቲዎች ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የዲጂታል ሊትረሲ የሥልጠናና ሰርተፊኬሽን ወርክሾፕ ከነሐሴ 11-14/2014 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በአሁኑ ጊዜ ሥራዎች በኮምፒውተር መታገዛቸው አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን የሚረዳና የወረቀት ሥራዎችን የሚቀንስ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ሀገር አገልግሎቶችን ኦንላይን የመስጠት ጅምሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ በተያዘው ዕቅድ መሠረት በቀጣይ 10 ዓመታት የመንግሥት አገልግሎቶች በአጠቃላይ ኦንላይን መሰጠት ሲጀምሩ ባለጉዳዮች በያሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሀገራዊ ግቡን በማሳካት ካደጉት ሀገራት ጋር ለመቀራረብና ሁሉም ሰው የኮምፒውተር ተጠቃሚ እንዲሆን መሰል ሥልጠናዎች ወሳኝ በመሆናቸው የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ሥልጠናውን መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንትና የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በበኩላቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከዩኒቨርሲቲው የምርምር ዘርፍና መማር ማስተማር ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለሥልጠናው ከቀላል አቀራረብ ጀምሮ ከፍተኛ ዕውቀት ማስጨበጥ በሚችል ደረጃ ሞጁሎች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቷ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችም ሆኑ ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው መሠልጠን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ/ICT/ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ታደሰ ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲዎች በላከው መመሪያ መሠረት ኦንላይን የማስተማሪያ ሞጁሎችንና የአሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዝግጅት ምዕራፍ ያከናወናቸው ተግባራት በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች መገምገማቸውንና ወርክሾፑ በቀጣዩ 2015 ዓ/ም ወደ ሥራ ለመግባት የመክፈቻ ፕሮግራም መሆኑንም አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

በዳይሬክቶሬቱ የአፕሊኬሽን ዴቬሎፕመንትና አድሚኒስትሬሽን ቡድን መሪ አቶ ሞገስ በኃይሉ ለሥልጠናዎቹ የጊዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቶ በ5 በመከፈል ለከፍተኛ አመራር፣ ለመካከለኛ አመራር፣ ለአስተዳደር ሠራተኞች፣ ለመምህራንና የቴክኒክ ረዳቶች፣ ለቢሮ ጸሐፊዎችና ረዳቶች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ቡድን መሪው ገለጻ ሥልጠናው በመሠረታዊ እና በከፍተኛ ደረጃዎች የሚሰጥ ሲሆን ምንም አይነት የዲጂታል ሊትረሲ ክሂሎት የሌለው ሠራተኛ መሠረታዊውን ሥልጠና ወስዶ በመመዘኛ ፈተናው ዝቅተኛውን የመመዘኛ ነጥብ 6.5 ከ 10 ሲያመጣ ወደ ቀጣይ ደረጃ የሚሸጋገር ይሆናል፡፡

መሠረታዊ የዲጂታል ሊትረሲ ክሂሎት አለኝ የሚል ሠራተኛ ተመዝግቦ ያለሥልጠና ፈተና በመውሰድ ዝቅተኛውን የመመዘኛ ነጥብ 6.5 ከ 10 ሲያመጣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር ሥልጠናውን የሚቀጥል ሲሆን ከፍተኛ ደረጃ ዲጂታል ሊትረሲን አጠናቆ ዝቅተኛውን የመመዘኛ ነጥብ 6.5 ከ10 የሚያመጣ ሠራተኛ ሥልጠናውን በሚገባ ማጠናቀቁን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት እንደሚያገኝ አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡ መሠረታዊ የዲጂታል ሊትረሲ መመዘኛ ነጥብን ለማያሟሉ ሠራተኞች ተጨማሪ ዕድል የማይሰጥ ሲሆን ለከፍተኛ ዲጂታል ሊትረሲ ሠልጣኞች አንድ ተጨማሪ እድል ይኖራቸዋልም ብለዋል፡፡

በወርክሾፑ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት