Print

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች በካምባ፣ ገረሴ፣ ቆላ ሼሌ፣ ብርብር፣ ዋጂፎ፣ ቦዲቲና አረካ ጤና ጣቢያዎች በቡድን ሥልጠና ፕሮግራም የቆዩበትን የመስክ ሪፖርት የኮሌጁ ገምጋሚ መምህራን በተገኙበት ነሐሴ 16/2014 ዓ/ም አቅርበዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኮሌጁ ቺፍ አካዳሚክ ዳይሬክተርና የቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ ረ/ፕ ተክሉ ተሾመ በሕክምናና ጤና ትምህርት ውስጥ የተግባር ልምምድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ በመሆኑ ተማሪዎች ከ2ኛ ዓመት ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ለተግባር ልምምድ ወደ ጤና ተቋማት እንደሚላኩ ተናግረዋል፡፡ የቡድን ሥልጠና ፕሮግራም ከተለያዩ ትምህርት መስኮች የተወጣጡ ተመራቂ ተማሪዎች በጋራ ለተግባር ልምምድ ወደ ጤና ተቋማት የሚላኩበት ፕሮግራም በመሆኑ ከሌሎች የተግባር ልምምድ ዓይነቶች የተለየ ያደርገዋል ያሉት አካዳሚክ ዳይሬክተሩ ተማሪዎች ወደ ሥራው ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት በትብብር የመሥራት መንፈስን፣ የእርስ በእርስ የዕውቀትና ልምድ ልውውጥን እንዲሁም ወደ ፊት የሚሠሩባቸው ተቋማትና የሥራ አካባቢን ከተግዳሮቶቻቸው ጋር እንዲለማመዱ ከማድረግ አንፃር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኮሌጁ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ረ/ፕ ደስታ ሀብቱ ኮሌጁ ከ46 በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም ሌሎች ኢንደስትሪዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በትብብር እየሠራ መሆኑን ተናግረው በዚህም የኮሌጁ ተማሪዎች የተሻለ የተግባር ትምህርት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡ የዘንድሮው የቡድን ሥልጠና ፕሮግራም ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ የሕክምና ዶክትሬት ምሩቅ ተማሪዎች የተሳተፉበት መሆኑንና ተማሪዎቹ በቆይታቸው በቡድን ወደ ጤና ተቋማት ወርደው ከኅበረተሰብ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት አነስተኛ ፕሮጀክቶችን ቀርጸው መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በገረሴና ካምባ ያሠሯቸው አነስተኛ የውሃ ቦኖ ፕሮጀክቶች፣ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃዎች እና የሕክምና ተቋማቱን ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎችን ኃላፊው ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ ፕሮግራሙ በዋናነት የሚዘጋጀው ተማሪዎች በቡድን የመሥራት መንፈስን እንዲያጎለብቱ፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ የመሥራት ልምድን እንዲያካብቱ፣ እርስ በእርስና ከሌሎች ጋር ሊኖር የሚገባን የተግባቦት ክሂሎት እንዲያዳብሩ፣ ገሃዱን የሥራ ዓለም እንዲለማመዱና ከ4-7 ዓመታት በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር እንዲሞክሩ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህም አንፃር ተማሪዎቹ ለቀጣይ ሥራቸው አጋዥ ቁምነገሮችን ማግኘታቸውን ከሪፖርታቸውና ከዚህ ቀደም በተደረጉ የመስክ ምልከታዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

ከተማሪዎቹ መካከል በካምባ ጤና አጠበባቅ ጣቢያ የቆየችው የ‹‹Health Informatics›› ትምህርት ፕሮግራም ተመራቂ ተማሪ ሊያ ሽመልስ በቆይታቸው በጤና ጣቢያው በድንገተኛ፣ በእናቶች ማዋለጃ፣ በተመላላሽ ታካሚዎች፣ በላቦራቶሪዎችና በሌሎች ክፍሎች በመገኘት የሕክምና አገልግሎት እንደሰጡና በዚህም በርካታ ልምዶችን ማግኘታቸውን ተናግራለች፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ችግሮችን ለይተው ለማኅበረሰቡ የጤና ትምህርት መስጠታቸውን እንዲሁም በከተማው ፉዳሌ በተሰኘ ቀበሌ በሚገኝ መንደር ያለውን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፍ አነስተኛ ፕሮጀክት በመቅረጽ ኅብረተሰቡንና የተለያዩ አካላትን አስተባብሮ ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለማኅበረሰቡ አነስተኛ የቦኖ ውሃ ማሠራት መቻላቸውን ተናግራለች፡፡

በገረሴ ጤና ጣቢያ የቆየችው የሕክምና ተማሪ ዶ/ር ብሌን ታደሰ ከዚህ ቀደም ለተግባር ልምምድ ሲወጡ የአንድ ትምህርት መስክ ተማሪዎች ብቻ በአንድ ላይ እንደሚወጡ አስታውሳ በዚህኛው ፕሮግራም ከተለያዩ የትምህርት መስኮች የተወጣጡ በመሆናቸው ዕውቀትና ክሂሎት መለዋወጣቸውንና በጋራ የመሥራት ልምድ ማካበታቸውን ተናግራለች፡፡ በተጨማሪም ቆይታችን ወደ ፊት የምናገለግለውን ማኅበረሰብ ችግሮችና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች የተገነዘብንበት ነበር ያለችው ዶ/ር ብሌን በአጠቃላይ የነበረን የ1 ወር ቆይታ በእጅጉ ጠቃሚ ነበር ብላለች፡፡

በመስክ ፕሮግራሙ የቆዩ ተማሪዎች ከ340 በላይ የሚሆኑ ከሕክምና፣ ፋርማሲ፣ ማኅበረሰብ ጤና፣ ሚድዋይፍሪ፣ ነርሲንግ፣ አካባቢ ጤና፣ ጤና ኢንፎርማቲክስና ሜዲካል ላቦራቶሪ ትምህርት ፕሮግራሞች የተወጣጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡


የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት