Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹International Youth Fellowship›› ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በአእምሮ ቀረጻ(Mind Set) ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሐምሌ 30/2014 ዓ/ም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ 
ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የ‹‹International Youth Fellowship (IYF)›› ሊቀ መንበርና የአስተሳሰብ ቀረጻ አስተምህሮ/Mindset Education/ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ቾው ሱንግዋ/Dr Cho Sunghwa/ እንደተናገሩት IYF በተለይ የወጣቶችን አእምሮ በመቅረጽ ጤናማ፣ ብሩህ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ነገሮችን ለማዳመጥና ለመቀበል የተዘጋጁ እንዲሁም በሥራቸው ስኬታማና መሪ እንዲሆኑ የሚንቀሳቀስ ግብረ ሠናይ ድርጅት ነው፡፡

ዶ/ር ቾው ደቡብ ኮሪያ የአስተሳሰብ ቀረጻ ፅንሰ ሃሳብን ለሕዝቧ በሚገባ በማስገንዘቧና የሕዝቡ የሥራ ባህል እንዲቀየር በማድረጓ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት መቻሏን ጠቅሰው ይህን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በቀጣይነት በሚሰጠው ሥልጠና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነቱን ማካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ለሚያከናውናቸው ከትምህርት ጋር የተያያዙ ተግባራት ድጋፍ ማድረግ፣ ለመምህራን፣ ለተማሪዎችና ለአስተዳደር ሠራተኞች የአእምሮ ቀረጻ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ዩኒቨርሲቲው በሚፈልገው መልኩ ለሠልጣኞች ልዩ የመማሪያ ክፍሎች እንዲመቻቹ መደገፍ፣ ሥልጠናውን ላጠናቀቁ የምስክር ወረቀት ማዘጋጀት እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ማካሄድ በIYF በኩል የሚከናወኑ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ሠልጣኞች ሥልጠናውን እንዲወስዱ ማነቃቃትና ማዘጋጀት፣ አፈጻጸሙን የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል በመሰየም የሥልጠናውን ሁኔታ መከታተልና መገምገም እና ለሥልጠናው አስፈላጊ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን ማረጋገጥ በዩኒቨርሲቲው በኩል ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

ሥልጠናው በ2015 ዓ/ም ተጀምሮ ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን እንደየ ሁኔታው በወር ወይም በሳምንት 1 ጊዜ ለመስጠት መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ሥልጠናውን ለመከታተልና በቀጣይ በሀገሪቱ በአመራርነት ደረጃ ለመቀመጥ ፍላጎቱ ያላቸው ሥልጠናውን መውሰድ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት