Print

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከክርስቲያን ኤይድ/Christian Aid/ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ጥቃቶች ለመከላከልና የተሞከሩ ወይም የተፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስተካከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚያሳይ ፖሊሲ ዙሪያ ለዩኒቨርሲቲው ዳይሬክተሮችና ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች ከነሐሴ 19-20/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው ከክርስቲያን ኤይድ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሥራዎችን መሥራቱን አስታውሰው ሴፍጋርዲንግ ፖሊሲን አስመልክቶ የተሰጠው ሥልጠና ዩኒቨርሲቲው እንደ ተቋም ሁሉን ያማከለ ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጡን ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ ሴፍጋርዲንግ ፖሊሲ ከተለያዩ የውጭ ሀገር ተቋማት ጋር ትብብሮችን ለመፈጸም ቀዳሚና ዋና መስፈርት በመሆኑ በትኩረት ይዘጋጃል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ሥልጠናው እየተሠሩ ያሉና ወደ ፊትም የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር የሚያስችል ልምድ የተወሰደበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ቶሌራ ከሕግ አገልግሎት፣ ከሰው ሀብት አስተዳደር፣ ከሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች እንዲሁም ከምርምር ዘርፎች የተወጣጡ ሰባት አባላት ባሉት ኮሚቴ ፖሊሲው በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶና ተገምግሞ አገልግሎት ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የክርስቲያን ኤይድ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አሠልጣኝ ፋንታሁን ዓለሙ እንደገለጹት ድርጅታቸው በእንሰትና በአነስተኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ከዩኒቨርሲቲው ጋር እየሠሩ መሆኑን ገልጸው ድርጅታቸው አብሮ ከሚሠራባቸው ተቋማት ጋር በ‹‹Safeguarding Policy›› የመሥራት ግዴታ ስላለበት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸው ሴፍጋርዲንግ ፖሊሲ የሌላቸው ተቋማት ጋር የሚሠራ ከሆነ ስለ ድርጅቱ ሴፍጋርዲንግ ፖሊሲ አስመልክቶ ስምምነት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

የጥቃት አይነቶች፣ ደረጃዎች፣ ጥቃትን መጠበቅ፣ መከላከል፣ ሪፖርት ማድረግና ምላሽ አሰጣጥ፣ የሴፍጋርዲን ፖሊሲ ስታንዳርድ፣ የአስተማማኝ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አቀራረጽ፣ የአደጋ መቀነሻ ስልቶች፣ የመረጃ ማጋራት አስፈላጊነት፣ የግብረ መልስ አሰጣጥና የቅሬታ አፈታት መርሆዎች በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች የተወሰኑት ናቸው፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የተገኘው ልምድና ግንዛቤ ዩኒቨርሲቲው በሚቀርጻቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ላይ በቀጥታ ተግባራዊ ስለሚደረግ ሥልጠናው ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው ለሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የሚሰጥበት ሁኔታ ቢኖር በተለይ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካላትን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል ግንዛቤ የሚፈጥር በመሆኑ ታቅዶ እንዲተገበርም ጠይቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት