በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች ላይ ተመሥርቶ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ሥር በሚገኙ 10 ወረዳዎች ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን በጀርመን ልማት ባንክ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በGIZ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ በሚሸፈን ከ1.8 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የሚከናወንና ለ5 ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት /Sustainable Land Management Project/ ይፋ ሆኗል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ምርምሮች ወደ ማኅበረሰብ የሚወርዱና የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሁም ለሀገር ጭምር ፋይዳ ያላቸው እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው አሠራሮችን ዘርግቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በጫሞና ዓባያ ሐይቆች እና ተፋሰስ ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው ሲደረጉ የነበሩ የምርምር ሥራዎች ከዚህ አንፃር ተጠቃሾች ናቸው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ከችግሩ አንገብጋቢነት አንፃር የምርምር ውጤቶችን በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ ለሚመለከታቸው አካላት ለማሳወቅ በመቻሉ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሚሆን ግዙፍ ፕሮጀክት ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው እንደ ተቋም እንዲሁም የዘርፉ ተመራማሪ ያለመሰልቸት ለሚመለከታቸው የመንግሥትና ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ማስገንዘብ በመቻላቸው ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር ሲሆን የፕሮጀክቱ መጀመር በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዩኒቨርሲቲውን ስም ከፍ የሚያደርግ ነውም ብለዋል፡፡

ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ በቀጣይ ጊዜያትም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ወደ መሬት መውረድ የሚችሉና የአካባቢውን ብሎም የሀገርን ችግር የሚቀርፉ እንዲሁም የረጂ ደርጅቶችን ትኩረት መሳብ የሚችሉ መሰል ምርምሮችን ከማከናወን ባሻገር የምርምር ውጤቶችንና ጭብጦችን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሚመለከታቸው የሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ለማስገንዘብ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

የAMU-IUC ፕሮግራም ኃላፊና የውሃ ሥነ ምኅዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በበኩላቸው የ3ኛ ዲግሪ የመመረቂያ ሥራቸውን የዓባያና ጫሞ ሐይቆች የምግብ ሰንሰለት ላይ በማተኮር እንዳከናወኑ ተናግረው በዚህም የተገኘው ውጤት በእጀጉ አስደንጋጭ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ የዓባያ ሐይቅ የምግብ ሰንሰለት በእጅጉ እንደተዛባና ጫሞ ሐይቅም በፍጥነት ሥራዎች ካልተሠሩ የዓባያ ዕጣ ፈንታ ሊደርሰው እንደሚችል ‹‹A Call to Action: Strong Long-term Immunological Changes in the Two Largest 2 Ethiopian Rift Valley Lakes, Abaya and Chamo›› በሚል ርዕስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች በማሳተም ለዓለም ለማሳወቅ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም አውስተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በ ‹‹IUC ፕሮጀክት 6›› በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ዙሪያ የተደረጉ ተጨማሪ ጥናቶችንና ግኝቶችን በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ ለሚመለከታቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት በተደጋጋሚ የማሳወቅ ጥረቶች መደረጋቸው ለፕሮጀክቱ መገኘት ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተም ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር ሐይቆችን መሠረት አድርጎ የሚሠራ በዓይነቱ የመጀመሪያው ፓይለት ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 25 ሚሊየን ዩሮ ከጀርመን ልማት ባንክ፣ 5.1 ሚሊየን ዩሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም 3.6 ሚሊየን ዩሮ በGIZ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚሸፈን ሲሆን ይህም ወደ ብር ሲቀየር ከ1.8 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑን ዶ/ር ፋሲል ጠቁመዋል፡፡ በሐይቁ ተፋሰሶች በሚገኙ 10 ወረዳዎች በጥናቱ በተቀመጠውና በተዘጋጀው ሞዴል መሠረት ሳይንሳዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ማከናወን የፕሮጀክቱ ዋነኛ ተግባር ሲሆን ሌሎች የአረንጓዴ ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና በፈር ዞኖችን/Buffer Zone/ የመለየት ሥራዎችም በፕሮጀክቱ ይከናወናሉ ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እውን ሆኖ ማየታቸው በእጀጉ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል ሐይቅን ከተፋሰሱ ለይቶ ማየት ስለማይቻል ተፋሰሱ ላይ በፕሮጀክቱ አማካኝነት የሚሠሩ ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ወደ ሐይቁ የሚገባውን ደለል በማስቀረት የሐይቁን፣ በሥሩ የሚገኙትን እንዲሁም የአካባቢውን ብዝሃ ሕይወት ከመጥፋት የሚታደግ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በእጅጉ የሚጠቅም እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የጀርመን ልማት ባንክ ከኢፌዴሪ ፋይናንስ እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የውል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ፕሮጀክቱ ይፋ በሚደረግበት ሥነ ሥርዓት ላይ የ10ሩ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች፣ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የፕሮጀክቱን የሥራ ሂደትና አፈጻጸም የመገምገምና የመፈተሽ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት