የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን/The United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR) ጋር ባደረገው ስምምነት ኮንሶ፣ ደራሼ እና አሌ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎችና መብታቸውን ለማስከበር አቅም ለሚያንሳቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ ድጋፍ ለማድረግ ከመጋቢት 2014 ዓ/ም ጀምሮ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ‹‹UNHCR-Arba Minch University Project›› የጋራ ፕሮጀክት አስጀምሯል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ እንየው ደረሰ እንደገለጹት ፍትሕ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ አቅም ለሌላቸው ዜጎች እና ቡድኖች የሕግ ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ ወክሎ በመከራከር፣ በሕግ ምክር፣ የተለያዩ አቤቱታዎችን በማዘጋጀት እና በንቃተ ሕግ ትምህርቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ዲኑ ዩኒቨርሲቲው ለረዥም ዓመታት ያለማቋረጥ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው ከዩኒቨርሲቲው ባሻገር በስደተኞችና በፍትሕ ላይ የሚሠሩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችን እገዛ በማግኘት ማዕከላቱ በባለሙያ፣ በግብዓትና በገንዘብ እንዲደገፉና የአገልግሎት ተደራሽነቱና የማኅበረሰብ ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል የሕግ ት/ቤት ፕሮጀክቶች ላይ የሚሠራ የራሱን ቡድን አዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

ከኮሚሽኑ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በተለይ ተፈናቃይ ወገኖች ባሉበት ኮንሶ፣ ደራሼና አሌ አካባቢዎች በአራት ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ቢሮዎችን ማደራጀት፣ የሠራተኛ ቅጥር፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ የመከራከሪያ ወጪን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በፕሮጀክቱ የሚደገፍ መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከፍተኛ በጀት መድቦ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚሠራ የጠቀሱት ዲኑ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረውን ሥራ በማሳደግና ተሞክሮውን በሌሎች አካባቢዎች ወዳሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት በማዳረስ ሁሉም ማዕከላት በኮሚሽኑና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚደገፉ ሆነው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ለሥራው ስኬት በየአካባቢው ለአገልግሎት ማዕከልነት የሚውሉ ቢሮዎችን በመስጠት ፍ/ቤቶችና የፍትሕ አካላት ዋነኛ አጋር መሆናቸውንም አቶ እንየው ገልጸዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ወርቁ በበኩላቸው የጫሞ ካምፓስ የሕግ ት/ቤት ማስተባበሪያ ጽ/ቤትን ጨምሮ፣ በአርባ ምንጭ ከተማ፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ፣ ጨንቻ፣ ም/ዓባያ፣ ሳውላ፣ ዳራ ማሎ፣ ጊዶሌ፣ ኮንሶ፣ ኮልሜ እና አሌ በሚገኙ 12 ማዕከላት በተለይም ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ፍትሕን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረትና ተደራሽነት ለማገዝ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከ2011-2014 ዓ/ም 229 መዝገቦችን ወክለን ተከራክረናል ያሉት ኃላፊው በወከልናቸው መዝገቦች የመርታት ምጣኔው 99.9 በመቶ ነው ብለዋል፡፡ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀምን ለአብነት በመጥቀስ 5,025 የሕግ ምክርና ለ8 ሺህ የማኅበረሰብ ክፍሎች የንቃተ ሕግ ትምህርቶች መሰጠታቸውን እንዲሁም ለ1,025 ተገልጋዮች ለተለያዩ ፍ/ቤቶች የሚቀርቡ አቤቱታዎች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዳኛቸው ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ነፃ የሕግ ድጋፍ ማዕከል በሌለው አካባቢ ማዕከል እንዲከፍት፣ ተቋርጠው የነበሩትን እንዲያስቀጥልና ነባሮቹን ማዕከላት በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስና በገንዘብ እንዲያደራጅ አስችሎታል፡፡ በፕሮጀክቱ አማካኝነት በወር 500 በዓመት 6 ሺህ ተገልጋዮችን ለመድረስ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን የንቃተ ሕግ ትምህርት፣ የሕግ ምክር፣ ማስታረቅ፣ ወክሎ መከራከር፣ ለፍርድ ቤትና ለአስተዳደር አካላት የሚቀርቡ ክስ፣ መልስ፣ ይግባኝ፣ የሰበር አቤቱታና የመሳሰሉትን ማዘጋጀት እንዲሁም የመታወቂያ ወረቀት፣ የይዞታ ማረጋገጫና የመሳሰሉ የሕግ ሰነዶችን እንዲያገኙ ማድረግና መሰል አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡

አገልግሎቱ የሚሰጠው በዋናነት ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግ ሲሆን ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞች፣ የሕግ ታራሚዎች እንዲሁም ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ጋር አብረው የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አቶ ዳኛቸው ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ በእስከ አሁን ቆይታው በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ 2,000 የሚሆኑ ተገልጋዮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ዳኛቸው ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ኮሚሽኑ 60 ሺህ ዶላር (2.8 ሚሊየን ብር) የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ፍትሕን ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተከታታይና ቋሚ ፕሮግራሞችን የሚጠይቅ በመሆኑ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም እየታየ ቀጣይነት የሚኖረውና በጀቱም የሚያድግ ይሆናል ብለዋል፡፡

የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት አቶ ሙሃባ ቀውያ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በበርካታ ጉዳዮች በጋራ መሥራታቸው ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ለማምጣት እንደረዳቸው ተናግረው በፕሮጀክቱ በዞኑ ካራት ከተማ እና ከከተማው በ40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ኮልሜ ክላስተር በተቋቋሙት ነፃ የሕግ ድጋፍ ማዕከላት የሚሰጡት ድጋፎች ፍ/ቤቱ የሚሠራውን ፍትሕን የማረጋገጥ ሥራ በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ ጠበቆች 50 ሰዓት ነፃ አገልግሎት እንዲሰጡ በሚያዝዘው መመሪያ መሠረት ከዚህ ቀደም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ትእዛዝ ቢሰጥም በሙሉ አቅምና እንደ ባለጉዳዩ ሆኖ በአግባቡ የመከራከር ሂደቱ ደካማ በመሆኑና በሌሎችም ምክንያቶች ውጤታማ አልነበረም፡፡ የዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች ከመጡ ወዲህ አገልግሎቱ በእጅጉ መሻሻሉን የገለጹት አቶ ሙሃባ ስለ አገልግሎቱ የሚሰጠውን መረጃ ሰምቶ የሚመጣው ኅብረተሰብ ቁጥር ማደጉን ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ቆሞ ለመከራከርና ፍትሕ ለማግኘት ያለ ገንዘብ እንደማይቻል የሚታመነውን አስተሳሰብ ለመቅረፍም ችሏል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለፍ/ቤቱ ዳኞች፣ ሬጂስትራሮችና ዐቃቤያን ሕግ ከፍ/ቤቱ የዕለት ከዕለት መዝገቦች ውስጥ በማይጠፉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናዎች በመስጠት ፍትሕን በማስፈጸም ሂደት በተግባር የሚያከናውኑት በሕግ ከተቀመጠው ጋር እንዲስማማ እገዛ ማድረጉን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናዎቹን በነጻ ማግኘታችን ፍ/ቤቱ ባለሙያዎቹን ለማብቃት ሊያወጣ የሚችለውን ገንዘብ ለሌላ አገልግሎት እንዲያውል አድርጎታል ያሉት ፕሬዝደንቱ ዳኞችና ዓቃቤያን ሕግ ሕጉን ቢያውቁትም ሥልጠናው እይታቸውን እንዲያስተካክሉና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ አግዟቸዋል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮንሶ ነፃ የሕግ ድጋፍ ማዕከል የሕግ ባለሙያ ወ/ሪት የምሥራች ግርማ በማዕከሉ የሕግ ማማከር፣ ወክሎ መከራከር እንዲሁም ክስ፣ የክስ መልስ፣ ይግባኝና የመሳሰሉ የሕግ አቤቱታዎች ማዘጋጀት የመሳሰሉ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ገልጻ ችሎት የሚመጡ ተገልጋዮች በሳምንት 2 ቀን እንዲሁም በሳምንት አንዴ በየወረዳዎቹና በቀበሌያት በሕዝብ መሰባሰቢያ ቦታዎች የንቃተ ሕግ ትምህርቶች ያገኛሉ ብላለች፡፡ ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ ስለ አገልግሎቱ መረጃ እንዳለውና ከሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ጋር ትስስር በመፍጠር ሴቶች የሕግ ድጋፍ ሲፈልጉ ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ ባለሙያዋ ተናግራለች፡፡ ፕሮጀክቱ ሥራ በጀመረባቸው ያለፉት ሁለት ወራት ወክሎ በመከራከር በሂደት ላይ ያሉ 6 መዝገቦችን መያዛቸውን የጠቀሰችው ባለሙያዋ ስለ አገልግሎቱ ዩኒቨርሲቲው የወረዳና የቀበሌ አመራሮችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን በማሳተፍ ሰፋ ባለ መልኩ የማስተወዋወቅ ሥራ ቢሠራ በተሻለ ሁኔታ በርካታ ማኅበረሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብላለች፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮልሜ ክላስተር ነፃ የሕግ ድጋፍ ማዕከል የሕግ ባለሙያ ወ/ሪት የንጋትወርቅ ጌቱ በአካባቢው ከነበረው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ሥራው በቅርቡ መጀመሩን ገልጻ ስለ አገልግሎቱ ግንዛቤ ለመፍጠር የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ምንም እንኳ አካባቢው ለትራንስፖርት አመቺ ባይሆንም ወደተለያዩ የስደተኞች የሰፈራ ጣቢያዎች ተንቀሳቅሰው እንደሚሠሩና ኅብረተሰቡም በአገልግሎቱ ደስተኛ መሆኑን ባለሙያዋ ገልጻለች፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት