Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ከተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት /Food and Agriculture Organization/ ደቡብ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር የሽፈራው/ሞሪንጋ ተክል ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል፣ ግብይቱን ማሳደግ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲሁም ዘርፉን በተሻለ ሁኔታ ማጠናከር ዙሪያ ከተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ለተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ከነሐሴ 18-20/2014 ዓ/ም የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ብርሃኑ ለማ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ ሠልጣኞች በሞሪንጋ ምርትና ምርታማነት፣ በስነ-ምግብ እና ግብይት ላይ ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ እንዲያሳድጉ፣ ያገኙትን ዕውቀት በአካባቢያቸው ለሚገኙ የሞሪንጋ አምራች ማኅበረሰብ ማካፈል እንዲችሉ እና ነባሩን የሞሪንጋ እሴት ሰንሰለት ማዘመንና በዘርፉ አዲስ አቅም መፍጠር ነው፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ አክለውም የሞሪንጋ ተክል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚፈለጉ ሁለገብ ተክሎች መካከል አንዱና አሚኖ አሲድ፣ ቫይታሚን፣ የተለያዩ ማዕድናትና ሴሊኒየም የበለፀገ መሆኑን ጠቅሰው ለሰው ልጆች ምግብነት፣ ለመድኃኒትነት፣ ለሳሙና መሥሪያነት እና ለእንስሳት መኖ በመሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ የሞሪንጋ ተክል ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር በሀገራችን በዘርፉ ብዙ እንዳልተሠራበት ጠቁመው ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ምርትና ምርታማነት በዘላቂ ሁኔታ አለማደግ፣ በተክሉ አያያዝ ዙሪያ ያሉ ችግሮች፣ የተክሉ በተባይና በበሽታ መጠቃትና የግብይት ሰንሰለቱ በተደራጀ ሁኔታ አለመካሄዱ ዋነኛዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  ምርቱ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በስፋት በምግብነት የሚታወቅ ከመሆኑም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በማስተማርና ምርምሮችን በማካሄድ የረዥም ዓመት ልምድ ያለው ተቋም በመሆኑ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን እንዲያንቀሳቅስና ከድርጅቱ ጋር በጋራ እንዲሠራ መመረጡን ዶ/ር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል የሞሪንጋ ፕሮጀክት እሴት ሰንሰለት ልማት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሞገስ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ከተባበሩት መንግሥታት የኢንደስትሪ ልማት ተቋም /United Nation Industrial Development Organization/ እና ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በክልሉ የሞሪንጋ ተክልን ለማስፋፋትና ለማጠናከር እየሠሩ ሲሆን ድርጅቱ በክልሉ ለሞሪንጋ ምርት አመቺ የሆኑ 7 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን መርጦ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ዘርፉን ለማስፋትና ሞሪንጋን ከምግብነት ባለፈ ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋልና ወደ ገንዘብ በመቀየር የአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይ ሴቶችና እናቶች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እና ሌሎች ተቋማትና ባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ በወዘቃ የሞሪንጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እየተገነባ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡

በሥልጠናው የሽፈራው/ሞሪንጋ ተክል ምንነት፣ ተክሉ ያለው የምግብና የመድኃኒትነት ይዘት፣ ተክሉ የሚፈልገው የአየር ፀባይ፣ የአፈር ሁኔታና አስፈላጊ ጥንቃቄዎችና ጥበቃዎች፣ የዘር አመራረጥ፣ ተስማሚ ችግኝ ጣቢያዎችን ማዘጋጀት፣ የድኅረ ምርት አያያዝ፣ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ያላቸው የገበያ ትሰስርና ተጠቃሚነት፣ የግብይትና የገበያ ሁኔታ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ የአግሮ ፎረስትሪ ቴክኖሎጂን መጠቀም ምርቱን ለማሳደግ የሚኖረው ፋይዳና መሰል ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡ በሥልጠናው መጨረሻም ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት