Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ዓ/ም በጋሞ ዞን ወረዳዎች ባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱና ክልሉ ከዕቅድ በላይ እንዲያሳካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከቱ ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ሐምሌ 30/2014 ዓ/ም የዋንጫና የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ አጋዥ ተቋማት ጋር የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ ሲሆን ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ በማዕድን አለኝታ ጥናቶች ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ በባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንደኛነት እንዲሸለም ዩኒቨርሲቲው እንደ ባለ ድርሻ አካል በመሥራት ቴክኒካዊና የሀብት ድጋፍ በማድረጉ ዕውቅና ሊሰጠው ችሏል፡፡

እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ባዮ ጋዝ ለምግብ ማብሰያነትና ለመብራት አገልግሎት በመዋል የማገዶ ወጪና የደን መጨፍጨፍን የሚቀንስ፣ ጭስ አልባ በመሆኑ በጭስ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን በማስወገድ ጤንነትን የሚያሻሽል፣ ለሥራ አጥ ሰዎች የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፣ የሴቶችን የሥራ ጫና የሚቀንስ፣ ለማዳበሪያነት የሚያገለግልና ሌሎችም በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታዎች ያሉት በመሆኑ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረጉ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በማይደርስባቸው አካባቢዎች በትምህርት ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች የፀሐይ ታዳሽ ኃይል በመዘርጋት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተሞክሮውን በማስፋት የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን በገበያ መር ሥርዓት በማልማትና በማስፋፋት የክልሉ ኅብረተሰብ ከቴክኖሎጂው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታዎች በማግኘት የኑሮ ደረጃው እንዲሻሻል ለማስቻል እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሶዴሳ ሶማ እንደገለጹት የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ በ2014 በጀት ዓመት ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን 5 ወረዳዎች፡- በምዕራብ ዓባያ፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ፣ ገረሴ፣ ጨንቻና ቁጫ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላትና ባለሙያዎችን በማሳተፍ 170 የባዮ ጋዝ ማብላያ ግንባታዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ችለዋል፡፡ ይህም በአማካይ ከ15-20 ዓመት ሊያገለግል እንደሚችል ዳይሬክተሩ ገልጸው በአጠቃላይ 1,290,793 (አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ሦስት) ብር ለግንባታው ወጪ መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የ1 ዓመት ቆይታ የማብላያ ግንባታው ጥራት በሚፈለገው ልክ እንዲሠራ የምርምር ማእከሉ ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ ማድረጋቸውንና ሂደቱ ለማኔጅመንት አባላት ቀርቦ ግምገማ እንደተደረገበትም ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት