እ.ኤ.አ በ2023 ‹‹Mandela Washington Fellowship›› ፕሮግራም ዙሪያ ከአሜሪካ ኤምባሲ በመጡ ባለሙያዎች ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ነሐሴ 25/2014 ዓ/ም ገለጻ ቀርቧል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ በ2014 የተጀመረና የ ‹‹Young African Leaders Initiative/YALI/ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ገለጻውን ያቀረቡት የአሜሪካ ኤምባሲ ባልደረባ አቶ ዳንኤል መስፍን ተናግረዋል፡፡ ፕሮግራሙ በየዓመቱ እድሜያቸው ከ25-35 ዓመት የሆኑ 700 ወጣት አፍሪካውያንን ወደ አሜሪካ በመውሰድ በሀገሪቱ በሚገኙ 28 የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ለ6 ሳምንታት የአመራርነት ሥልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ እስከ አሁን ባለው የፕሮግራሙ ሂደት 5,800 ያህል አፍሪካውያን የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳንኤል የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ምንም ዓይነት ክፍያ የማይጠየቅና በኦንላይን የተዘጋጀውን ማመልከቻ በአግባቡ መሙላት ብቻ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ለሠልጣኞች ከ6 ሳምንታት ሥልጠናው ባሻገር በአሜሪካ ሀገር የሚገኙ የተለያዩ ኢንደስትሪዎችን የመጎብኘትና የአሠራር ልምድ የማግኘት፣ ከወጣት አፍሪካዊ መሪዎች ጋር በሚደረግ ስብሰባ ላይ የመሳተፍ፣ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኙ የመንግሥት፣ የሲቪክ ማኅበራትና የንግድ ተቋማት መሪዎች ጋር የመገናኘትና ሌሎችም እድሎች እንደሚመቻቹላቸው አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዳንኤል በሕዝብ አገልግሎት፣ በንግድና በሲቪክ ድርጅቶች ውስጥ የተረጋገጠ የአመራርነት የተሻለ አፈጻጸም፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በበጎ ፈቃደኝነትና በማማከር ሥራ የተመዘገበ አፈጻጸም፣ በተለያዩ ቡድኖች ሥር ሆኖ በትብብር የመሥራትና የሌሎችን ሃሳብ የማክበር ችሎታ፣ ጠንካራ የማኅበራዊና የተግባቦት ችሎታ እንዲሁም ወደ መጣበት ሀገር በመመለስ ያገኘውን የአመራርነት ዕውቀት በመጠቀም ሀገሩንና ማኅበረሰቡን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ከውድደሩ መስፈርቶች መካከል ናቸው፡፡

በእለቱ እ.ኤ.አ በ2022 የእድሉ ተጠቃሚ የነበሩት ዶ/ር ምስክር ካሣሁን እድሉን እንዴት እንዳገኙ እና በቆይታቸው ያገኟቸውን ጥቅሞች፣ ልምድና ተሞክሮዎች ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት