Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ለዋናው ግቢ የተማሪዎች አገልግሎትና የቤተ መጻሕፍትና መረጃ አገልግሎት ሠራተኞች ሥራና አመለካከት፣ ሕይወትና የአእምሮ ውቅር በሚል ርዕስ ከነሐሴ 25-27/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አሠልጣኝ አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለጹት ሥልጠናው በዋናነት በሰው አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ያተኮረና ራሱን ያወቀ፣ ከራሱ ጋር የታረቀ፣ ዓላማ መር ሕይወት ያለው፣ ሀገሩን የሚወድ፣ ስለ ሀገሩ ኃላፊነት የሚሰማው እና ለተቋሙ አቅምና ጉልበት የሚሆን ዜጋ ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው፡፡

የሕይወት ምንነት፣ የሕይወት ምርጫ፣ የአእምሮ ውቅር ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ አስተሳሰብና የአስተሳሰብ ለውጥ፣ ሰብእናና ጠባይ፣ የሰው ልጅ ራዕይና ዓላማ፣ የአመራር ክሂሎት እንደዲሁም የግል ሕይወትን ማሳካትና ለውጥን ማስቀጠል ለራስ፣ ለተቋምና ለሀገር ያለው ፋይዳ በሥልጠናው ከተዳሰሱ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ራሳችንን እንድናይና ክፍተቶቻችንን እንድንረዳ ትልቅ እድል የፈጠረና የሕይወት ለውጥ ለማምጣት ግብዓት ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ የተሰጣቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት