የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ሀብትና መስኖ ምኅንድስና እና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሜካኒካል ምኅንድስና ፋከልቲዎች ነሐሴ 27/2014 ዓ/ም የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃ ግብር የሥርዓተ ትምህርት የውጭ ግምገማ አካሂደዋል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ለ2ኛና 3ኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮች ትኩረት መሰጠት እንዳለበት የተናገሩት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ለሥርዓተ ትምህርት ግምገማ የቀረቡት ፕሮግራሞች ሀገራችን ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም ብሎም ወደ ኢንደስትሪው ዘርፍ ለምታደርገው ሽግግር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ከሰው ኃይል፣ ከቤተ ሙከራና ቤተ መጻሕፍት አንጻር መሟላት ለሚገባቸው ነገሮች ትኩረት በመስጠትና በግምገማው የተነሱ ገንቢ ሃሳቦችን በማካተት መርሃ ግብሮቹ ውጤታማ እንዲሆኑ እንሠራለንም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል እንደገለጹት ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት የታደለች ሀገር ብትሆንም የአቅም ውስንነቶች ሀብቷን በአግባቡ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቷ እንዳትጠቀም አድርጓታል፡፡ ሃይድሮሎጂ በውሃ ምኅንድስና ጥናት ውስጥ ካሉ አስፈላጊ የትምህርት መስኮች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሩ በዘርፉ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃ ግብር ማስጀመር ሀገራችን ያላትን የውሃ አቅም ለማወቅና ጥቅም ላይ ለማዋል የፖሊሲ አቅጫዎችን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በሀገር ደረጃ ያለንን የብረት ማዕድን ሀብት ለማልማትና የኢንደስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ የሠለጠነ የሰው ኃይል የሚያስፈልገን በመሆኑ ዘርፉን በሰው ኃይልና በምርምር ለመደገፍ በማቴሪያል ምኅንድስና የ3ኛ ዲግሪ መርሃ ግብር መጀመሩ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ የውጭ ገምጋሚ ዶ/ር ጌትነት አሥራት በበኩላቸው በሀገሪቱ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ የማኑፋክቸሪንግና የብረታ ብረት ኢንደስትሪ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ፕሮግራሞቹ ወቅቱ በሚፈልገውና በስፋት ባልተሠራበት ዘርፍ ላይ የተቀረጹ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ፣ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ፣ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አልሙናይ አባላት ዶ/ር ካሳ ታደለና ዶ/ር ፋሲካው አጥናው፣ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መዝገቡ በላይ እና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡

                                                                                                                                                                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት