Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን/The United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR) ቢሮ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በተፈናቃይ ሰዎች የሕግ ጥበቃ፣ በሴቶችና ሕፃናት መብት ጥበቃ፣ በንብረት ሕግ እንዲሁም በካምፓላ ስምምነት ዙሪያ በአሌ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 17 ቀበሌያት ለተወጣጡ የማኅበራዊ፣ የወረዳና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ መርማሪ ፖሊሶች፣ የፍትሕ ቢሮ ዐቃቤያን ሕግ እንዲሁም ከሴቶችና ሕፃናት እና ከልዩ ወረዳው ምክር ቤት ለተወጣጡ 30 ሠልጣኞች ከነሐሴ 30 - ጳጉሜ 1/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ


የአሌ ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ መንግሥቱ አምቡ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ኋላ ቀር የሆኑና የሕግ ንቃት ተደራሽ ያልሆኑባቸው አካባቢዎችን በማዳረስ ዜጎች በሕግ የተሰጣቸውን መብት አውቀው ለመብታቸው መከራከር እንዲችሉና ሌሎችም እንዲከራከሩላቸው ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ከዚህ ቀደም በቤተሰብና በውርስ ሕግ ዙሪያ ዩኒቨርሲተው ሥልጠና የሰጠ መሆኑን አስታውሰው በአካባቢው ያለውን ችግር በመገንዘብ ከሚመለከተው አካል ጋር ግንኙነት በመፍጠር ተፈናቃዮች፣ አረጋውያን፣ ሴቶችና ሕፃናት ለችግር እንዳይጋለጡ ከሕግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ እያመቻቹ ነው ብለዋል፡፡


አክለውም ሥልጠናው የፍትሕ አካላትን ጨምሮ ገጠር አካባቢ ያሉ ባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈ መሆኑ ወደ ታች ወርደው ተገልጋዮች እንዴት መብታቸውን መጠየቅና ማስከበር እንዳለባቸው ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚረዳ ከመሆኑም ባሻገር ዳኞች የክስ ጭብጦችን በቀላሉ እንዲለዩና አከራክረው እንዲወስኑ ብሎም የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞች ሥልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያንን በመደገፍ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ሊያሳዩ እንደሚገባ እና ከፍትሕ አካላቱም ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡


የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር እንየው ደረሰ በሰጡት ሥልጠና እንደገለጹት ሴቶች እንደ ዜጋ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሕግ ቢረጋገጥላቸውም ጾታቸውን መሠረት ያደረገ የቆየ አስተሳሰብና ባህል እንቅፋት ሲሆንባቸው ቆይቷል፡፡ ይህ በሴቶች ላይ የሚደርሰው አስከፊ በደል ዕውቅና አግኝቶ የማስተካከያ መንገድ ካልተበጀለት ሴቶች ለዜጎች በተደነገጉ ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብቶች ብቻ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሴቶችን ሰብአዊ መብት ከመጻረራቸውም በላይ ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ እንዳይሳተፉ እንቅፋት በመሆናቸው መንግሥት ግዴታ ገብቶ ልማዶቹ በሕግ እንዲከለከሉ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንዲቀመጡ መደረጉን ዲኑ ጠቁመዋል፡፡


መ/ር እንየው አክለውም ጾታና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከፍላጎት ውጪ የሆኑ ማንኛውም  የገንዘብ፣ የኢኮኖሚ፣ የአካል፣ የስነ ልቦና፣ የቤተሰብ ጥቃቶች እንዲሁም  በሴቶችና በወንዶች መካከል እኩል የሀብት ክፍፍል አለመኖር መሆናቸውን ጠቁመው በዚህ ረገድ የሚደርሰውን ጥቃት ታግሎ መቀነስና ማስቆም እንዲቻል ሁሉም ባገኘው አጋጣሚ ማኅበረሰቡን በማስተማርና ግንዛቤውን በማስፋት የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡  

የሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ዳኛቸው ወርቁ በበኩላቸው በንብረት ሕግ እና በደቡብ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የንብረት ሕግ በአንድ ግዙፋዊነት ባለው ወይም በሌለው ቁስ ላይ የንብረት መብት እንዴት እንደሚገኝ፣ እንደሚተላለፍና እንደሚቋረጥ የሚደነግግ የፍትሐብሔር ሕግ ዘርፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡


እንደ መ/ር ዳኛቸው ገለጻ የንብረት መብት ጥበቃ ለአንድ ግለሰብ ብሎም ማኅበረሰብ እና ሀገር ያለው ሚና እጅግ ወሳኝ እንደመሆኑ የሀገራችን ሕገ መንግሥት በግልጽ ከለላ ሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረቱ እንደሚከበርለት፣ ሕግን መሠረት አድርጎ ንብረት የመያዝ እና የመጠቀም መብት እንዳለው እንዲሁም የሌሎችን መብት ሳይነካ ንብረቱን ማስተላለፍ እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡


አክለውም አንድ ሰው በአንድ ንብረት ላይ ይዞታ አለው የሚባለው ንብረቱን በእጁ አድርጎ ሲያዝዝበት ሲሆን ንብረቱን በግልጽ  በቁጥጥር ስር በማድረግ መጠቀምና መገልገል ይገባዋል ብለዋል፡፡ የአንድ ንብረት ባለቤት ሆኖ ለመጠቀም ወሳኝ የሆነው የይዞታ መብት ጥበቃ ካልተደረገለት ትርጉም እንደሚያጣና ይህም ማኅበራዊ አለመረጋጋትን፣ ፖለቲካዊ ቀውስን እና ኢኮኖሚያዊ መራቆትን እንደሚያስከትል ጠቁመዋል፡፡


በተጨማሪም የይዞታ መብት በሕግ ጥበቃ ያስፈለገበት ምክንያትና የማስከበሪያ መንገዶች፣ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር፣ ተፈናቃዮች በንብረታቸው ረገድ ያላቸው ጥበቃ፣ የካምፓላ ስምምነት ምንነት የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች በሥልጠናው ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

   
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ወሳኝና ክፍተቶችን በመቅረፍ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረው በአካባቢው ለሴቶች ካለው የግንዛቤ ክፍተትና የአመለካከት ችግር የተነሳ ሴቶች ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ ወደየአካባቢያችን በመሄድና ለማኅበረሰቡ ትምህርት በመስጠት ሴቶች ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እንጥራለን ብለዋል፡፡ ሁሉም ማኅበረሰብ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ችግሩን በጋራ ለመፍታት እንዲቻል ሥልጠናው ለሌሎች የሚዳረስበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቀዋል፡፡


በተጨማሪም የንብረት ሕግ እና የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ እንዲሁም በተፈናቃዮችና በሕፃናት መብቶች ዙሪያ የተሰጡ ሥልጠናዎች ጥሩ ግንዛቤን የፈጠረላቸውና ማኅበረሰቡን የሚያነቃ መሆኑን እንዲሁም መብታቸውን እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነው ብለዋል፡፡
                                                                                                                                                                                                                        የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት