አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ኤይድ/Christian Aid/ ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በካምባ ወረዳ ዲንጋሞ ቀበሌ ማይጸሌ ወንዝ ላይ የሚያስገነባው አነስተኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ የዲዛይንና ቅድመ ጥናት ሥራ ዙሪያ የክርስቲያን ኤይድ ኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎች፣ የፕሮጀክቱ አባላትና አማካሪ ቦርድ አባላት በተገኙበት ነሐሴ 25/2014 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል የሃይድሮፓወር ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ በየነ ፈዬ እንደገለጹት የአካባቢው ማኅበረሰብ የኃይል ፍላጎት እስከ 10 ኪ.ዋ ሲሆን የዲንጋሞ አነስተኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ደግሞ 13.76 ኪሎ ዋት ነው፡፡ ይህም ከ600 በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም ለተለያዩ የንግድ ድርጅቶች እና ለእህል ወፍጮ አገልግሎት ይውላል፡፡ እንደ አቶ በየነ ገለጻ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ  ይጀመራል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ አማካሪ ቦርድ አባል ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ ጀምሮ የዲዛይንና ሌሎች የቴክኒክ ሥራዎች በእቅዱ መሠረት እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀጣዮቹ 6 ወራት ሥራው ወደ መሬት የሚወርድበትና ከፍተኛ ዕውቀትና ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ የፕሮጀክቱ አባላት በስነ ልቦና፣ በዕውቀት እና  በጉልበት  ጠንካራ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበው የሚመለከታቸው አካላት ፕሮጀክቱን በሙሉ አቅማቸው እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክርስቲያን ኤይድ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ ደገፉ ጌታቸው ፕሮጀክቱ ከትልልቅ ወንዞች ባሻገር ትንንሽ ወንዞች ላይ በአነስተኛ በጀት አነስተኛ የኃይል ማመንጫ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ የሚሆን ነው ያሉት አቶ ደገፉ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ ይሆን ዘንድ ሥራዎችን በአግባቡ ሰንዶ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት